🔇Unmute
ጅግጅጋ ፤መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፡-ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰቡን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በጥናት እና ምርምር እያገዘ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሳ መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እና በሶማሌ ክልል ውኃ ቢሮ አዘጋጅነት ዓለም አቀፍ የውኃ ቀንን ምክንያት በማድረግ የምክክር መድረክ በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሳ መሐመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ውኃ ለማንኛውም ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም በዚህ ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎች በተለይ እንደ ሶማሌ ክልል ላሉ ቆላማ አካባቢዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲውም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከክልሉ ውኃ ቢሮና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል ተማሪዎችን በገጸ-ምድርና በከርስ-ምድር ውኃ ልማት ዘርፎች ማሰልጠንና ማስመረቅ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም በውኃ ሀብት ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ የጥናት እና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የውኃ እጥረት ያለባቸውን አካባቢዎችን በተለያዩ መንገዶች የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ውኃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ መሐመድ በበኩላቸው፤ መንግሥት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ሽፋን 51 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፣ በገጠርና በከተሞች ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት የውኃ አገልግሎት ተቋማትን የማስተዳደር አቅም ማጎልበት እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የውኃ ተጠቃሚነትን ማስፋፋት ትኩረት ሊያገኙ ይገባል ብለዋል።
የውኃ ፕሮጀክቶች በቋሚነት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የጥገናና የክትትል አቅምን ማሳደግ እና ኅብረተሰቡ በዝናብ ወቅት ውኃን የመቆጠብና የመጠቀም ግንዛቤው እንዲጎለብት መስራት ከባለድርሻ አከላት የሚጠበቅ መሆኑ ተመልክቷል።
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የአፋር ሰመራ ሁለተኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ወደ ሥራ መግባቱ በክልሉ የሚገኘውን ሰፊ የእንስሳት ሀ...
Apr 1, 2026
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ተቋማቸውን ለተገልጋዮች ምቹ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ...
Feb 28, 2025
ወልቂጤ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ጋር በመሬት ምልከታ እና በኮሙኒኬሽን ሳ...
Feb 28, 2025