አዳማ፤ ሀምሌ 12/2017(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በየዘርፉ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ መንግስት የተለያየ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
እየተካሄደ በሚገኘው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከጨፌው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት የዘርፍ መሪዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም በበጀት ዓመቱ የነበረውን እጥረት ለመፍታት 29 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሃፍት ለትምህርት ቤቶች እንዲከፋፈሉ መደረጉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በተያዘው እቅድ መሰረት መከናወኑን ገልጸው 31 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግም ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
የመምህራን እጥረትን ለመፍታትም 4 ሺህ መምህራን በተያዘው ክረምት ሰልጠነው ወደ ስራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ በግብርና ዘርፉም ውጤታማ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ናቸው።
በተለይም የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቁመው የግብርና ግብዓት አቅርቦቱም በተሻለ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የክልሉን ህዝብ የንጹህ ውኃ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ግንባታቸው የዘገዩ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማትን የማጠናቀቅ እንዲሁም የአዳዲስ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ግንባታም በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይም የክልሉ የመስኖና አርብቶ አደር ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ፣ በበጀት ዓመቱ የመስኖ አውታሮችን በፍጥነትና በጥራት ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።
በቢሮው አማካኝነት የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል ታስቦ በግንባታ ላይ የነበሩ 261 አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቁንም አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በግንባታ ላይ የሚገኙ እና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የበለጠ የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ 5 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገን እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ የክልሉ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሄለን ታምሩ ናቸው።
በበጀት ዓመቱ የበርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እና ድልድዮች እንዲሁም የመናኸሪያዎች ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን አስረድተዋል።
ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት የሆኑ ችግሮችንም በተቀናጀ መንገድ መፍታት መቻሉንም ኃላፊዋ ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ተቋማቸውን ለተገልጋዮች ምቹ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ...
Feb 28, 2025
ወልቂጤ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ጋር በመሬት ምልከታ እና በኮሙኒኬሽን ሳ...
Feb 28, 2025
ጋምቤላ ፤የካቲት 17/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ እርም...
Feb 24, 2025