የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ በቡና እና ስንዴ ምርታማነት ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች የተሻለ ልምድ ወስደናል

Jul 31, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቡና እና ስንዴ ምርታማነት ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች የተሻለ ልምድ መውሰዳቸውን የዛምቢያ እና ናይጄሪያ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው ሁለተኛው አለም አቀፍ የምግብ-ሥርዓት ጉባዔ ትናንት ተጠናቋል።

በጉባኤው የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ የአለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች ፣አምራችና ላኪዎችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ከጉባዔው ተሳታፊዎች መካከል የዛምቢያና የናይጄሪያ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጸው፤ ይህንኑ ስኬት መስክ ድረስ ሄደው ማረጋገጣቸውን ነው የመሰከሩት።


የዛምቢያ የብሔራዊ የሥርዓተ-ምግብ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሙንታንጋ ካምፔንጌል (ዶ/ር) አገራቸው ከኢትዮጵያ የግብርና ሥራ በርካታ ልምዶችን መውሰዷን ነው ያስታወቁት።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗን ተከትሎ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባከናወነችው አመርቂ ተግባር ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ምርት በእጅጉ ማሳደግ መቻሏን አድንቀዋል።

ዛምቢያ ቡና አምራች ብትሆንም እንደ ኢትዮጵያ በብዛት የማምረት አቅም አለመገንባቷን ተናግረዋል።


ቡና ከምግብ-ሥርዓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖረውም ምርቱን በብዛት በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ከሚገኘው ገቢ የምግብ ፍላጎትን ማሟላት እንደሚቻል ነው ያነሱት።

በናይጄሪያ የጤናና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥርዓተ-ምግብ ዳይሬክተር ላዲዲ አይቡሲ የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ በርካታ ወጣቶችን ማሳተፉን መመልከታቸውን አንስተዋል።


አገራቸው በግብርና ዘርፉ በርካታ ወጣቶች እንዲሰማሩ ፍላጎት እንዳላትና ለዚህ ስኬት ከኢትዮጵያ ልምድ መውሰድ መቻላቸውን ነው የገለጹት።

የዛምቢያ የብሔራዊ የሥርዓተ-ምግብ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሙንታንጋ ካምፔንጌል (ዶ/ር) ስንዴ በበርካታ አገሮች ዋነኛ የምግብ ሰብል መሆኑን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ አገራቸው ዛምቢያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት አሁንም ድረስ ስንዴን ከውጭ እንደሚያስገቡ ነው ያስታወቁት።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከራሷ አልፋ ወደ ውጪ መላክ መጀመሯ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

እንደ ስነ-ምግብ ባለሙያዎቹ ገለጻ፣ በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማዳረስ አገራት አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች መደገፍ አለባቸው።

በዚህ ረገድ የተገኘው ምርት ለተጠቃሚው እስኪደርስ ያለውን ሰንሰለት ቀልጣፋ በማድረግ የምግብ-ስርዓት ሽግግርን ማፋጠን እንደሚገባ አንስተዋል።

ሁለተኛው የአለም የምግብ-ሥርዓት ጉባዔ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ሥራ በሚገባ ያሳየችበት መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.