የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ ሰላምን በማስፈንና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ለሌሎች የልማት ስራዎች መፋጠን መደላድልን እየፈጠረ ነው

Jul 25, 2025

IDOPRESS

ደብረ ማርቆስ፤ ሐምሌ 17/2017 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን በማስፈንና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የተሰራው ሥራ ለሌሎች የልማት ሥራዎች መፋጠን መደላድልን እየፈጠረ መምጣቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ115 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስተዳደሩ አስታውቋል።

የዞኑ አስተዳደር የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሄዷል።


የዞኑ አስተዳደር አማካሪ አቶ ሙሉቀን ቢያድግልኝ በመድረኩ እንደገጹት በበጀት ዓመቱ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በማጠናከር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ተሰርቷል።

በየደረጃው ሰላምን ለማስፈንና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የተሰራው ሥራ ለሌሎች የልማት ሥራዎች መፋጠን መደላድልን እየፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዞኑ የተገኘውን ሰላም በመጠቀም በበጀት ዓመቱ ለ115 ሺህ 747 ሥራ አጥ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራም በሄክታር ከ27 ኩንታል በታች የነበረውን ወደ 35 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ሲቪል ሰርቫንቱ የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ ከአድሎና ብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ አገልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ መምጣቱንም ገልጸዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አንዷለም በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የጤና መድህን አገልግሎትን በማስፋትና በሁሉም ቀበሌዎች የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በማሰማራት የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ መሰራቱን አመልክተዋል።

የዞኑ ስራና ስልጠና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አበጀ አላምረው በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ቅንጅታዊ አሰራርን በማዳበር በስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አውስተዋል።

በዚህም የስራ እድል ለመፍጠር ከታቀደው ውስጥ 76 በመቶ የሚሆነውን ለማሳካት መቻሉንም ተናግረዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ በዞኑ የሚገኙ ተቋማት ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.