የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በከተማ አስተዳደሩ የሌማት ትሩፋት ትግበራ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራ ተጨማሪ አቅምን ፈጥሯል

Jul 25, 2025

IDOPRESS

አዳማ ፤ሐምሌ 17/2017(ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ አስተዳደር የሌማት ትሩፋት ትግበራ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን የከተማዋ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ ለኢዜአ እንደገለጹት በአዳማ ከተማ ባለፉት ሶስት ዓመታት በዘመናዊ እንስሳት እርባታ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በሰብልና በፍራፍሬ ልማት ስራዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል።

በዚህም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሀብቶች ለሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተጨማሪ አቅም መፍጠራቸውን ተናግረዋል።


ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በከተማ ግብርና ለ35 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልፀዋል።

የስራ እድል ፈጠራውን ለማሳካትም በመንግስትና በማህበረሰቡ ተሳትፎ 2 ሺህ 500 ሼዶች መገንባታቸውንና የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞችና ዶሮዎች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል።


በዓሣ ሀብት ልማቱ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ስራ 154 የዓሳ ማራቢያ ኩሬዎችን በመገንባት ለወጣቶች ማስተላለፍ መቻሉን ተናግረዋል።


ዘመናዊ የንብ እርባታን ለማስፋፋትም ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት 11 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች እንዲሰራጩ መደረጉን አመልክተዋል።

የፍራፍሬ ልማትን ለማሳካት ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብና የአዋሽ ወንዝን በመጥለፍ በማህበር የተደራጁ አርሶ አደሮችና ወጣቶች በፓፓዬ፣ በሙዝ፣ በብርቱካንና በአቮካዶ ልማት ላይ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።


የከተማ አስተዳደሩ የስራ እድል ከፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል በወንጂ ኩሪፍቱ ክፍለ ከተማ የ''ዴይሊ ፊሽ ማህበር'' አባል ወጣት በዛወርቅ አጥላው ከአምስት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ጓደኞቹ ጋር በማህበር በመደራጀት በዓሣ እርባታ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጿል።

ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ በሰጣቸው 40 የዓሣ ኩሬዎች ውስጥ ከዝዋይ ሀይቅ ያስመጧቸውን የዓሳ ጫጩቶች እያረቡ መሆናቸውን አስረድቷል።


በከተማዋ ''የማትናደፍ ንብና የማር ምርት ማህበር'' ሊቀመንበር ዮናስ ገብረኪሮስ በበኩላቸው ከከተማ አስተዳደሩ በተረከቡት ሼድ ዘመናዊ፣ ባህላዊና የሽግግር ቀፎ ንብ ማነብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዓመቱም በሁለት ዙር ጥራቱን የጠበቀ እስከ 2 ሺህ 500 ኪሎ ግራም የሚደርስ ማር በማምረት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


ስራቸውን ለማስፋፋት የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀላቸው 5 ሺህ ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፍ የፕሮጀክት ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

በፕሮጀክቱ በ1 ሼድ እስከ 200 የንብ ቀፎ ማስተናገድ የሚያስችል ባለ አራት ወለል ህንጻ በመገንባት ''የንግስት ንብ እርባታና የንብ ምርምር ማእከል'' ለመገንባት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.