የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮ ቴሌኮም በዕድገት ስትራቴጂው ለዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል-ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ

Jul 25, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 17/ 2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም ለሦስት ዓመታት የተገበረው መሪ የዕድገት ስትራቴጂ ለዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፥ የኩባንያውን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የዕድገት ስትራቴጂውን ማጠቃለያ ሪፖርት ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።


ኢትዮ ቴሌኮም ከሦስት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የሚያሳደግ፣ ገቢውን ከፍ የሚያደርግ እና የደንበኞችን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሻሽል ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ከቴሌኮም ግንኙነት ባሻገር የፋይናንስ ስርዓቱ ዘመናዊ እና አካታች እንዲሆን በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከድምጽ ጥሪ፣ ከኢንተርኔት አገልግሎት፣ ከቫስ፣ ከመሠረተ ልማት ማጋራት፣ ከቴሌኮም ቁሳቁስ ሽያጭና ከሌሎች ምንጮች 162 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።

እንደ ቴሌ ብር፣ ቴሌ ገበያ እና የመሳሰሉት የዲጅታል የግብይት መተግበሪያዎችን በማስፋፋት የፋይናንስ ስርዓቱ ዘመናዊ እንዲሆንና የመንግስት ተቋማት አገልግሎት እንዲዘምን ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

መሪ የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂው ለዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው ያነሱት፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በ2017 በጀት ዓመት የቴሌኮም አገልግሎት ማስፋፊያዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፥ 16 ከተሞችን በ5 ጂ እና 512 ከተሞችን በ4ጂ ኔት ወርክ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በርካታ የሞባይል ጣቢያዎች መገንባታቸውን በማንሳት፥ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ሺህ በላይ የሞባይል ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በዚህም በመላ ሀገሪቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን የፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ነው የተናገሩት።

ኩባንያው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ማስፋፊያና የማሻሻያ ስራዎችን በማከናወን የአገልግሎት ተጠቃሚዎቹን ቁጥር 83 ነጥብ 2 ሚሊዮን ማድረሱን ገልጸዋል።

የቴሌ ብር፣የዘመን ገበያ እና መሰል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እያደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.