የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ህዳሴ

Jul 24, 2025

IDOPRESS

ድርቅ እና የደን መጨፍጨፍ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሲነሱ የቆዩ ችግሮች ናቸው።

ኢትዮጵያ ይህን ታሪክ ለመቀየር ቆርጣ ከተነሳች ዓመታት ተቆጥረዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ- ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአካባቢ ጥበቃና የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እንድትሆን ዋነኛ የለውጥ ሞተር ሆኗል።

በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ብዝሃ ህይወትን ወደ ቀደመ ስፍራው ለመመለስ፣ በርሃማነትን ለመከላከል፣ የደን ሽፋንን ለመጨመር እንዲሁም በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ጥረቶች አስተዋጽኦ እስከ ማበርከት ደርሷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦችና ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት በመሰናሰል ዘላቂና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት ትልም አለው።


ኢኒሼቲቩ ድንበር ተሻጋሪ ተጽእኖም ያለው ነው። አረንጓዴ ዐሻራ በደን መልሶ ማልማት አማካኝነት ዛፎችን ወደ ይዞታቸው በመመለስ ወደ አየር የሚለቀቁ በሚሊዮን ቶኖች የሚቆጠር ካርቦንዳይኦክሳይድ አምቆ በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካርቦንዳይኦክሳይድን ከከባቢ አየር የማስወገድና የማከማቸት ጥረት ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ካርቦንዳይኦክሳይድን አምቆ መያዝና ማከማቸት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።

ድንበር ተሻጋሪው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በአፍሪካ ቀንድ የመሬት መሸርሸርን እና የደን ሽፋንን በመጨመር በርሃማነትን ከመከላከል እንዲሁም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የራሱን በጎ ሚና ተጫውቷል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ ውይይቶች የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሯ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቀነስ በኩል እያበረከተ ያለው ሚና እውቅና የተሰጠው ነው።

መልከ ብዙው አረንጓዴ ዐሻራ በአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አዲስ አማራጭን ይዞ የመጣ እንደሆነም ይጠቀሳል።

ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና አካባቢ ጥበቃ ስራ የውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ ከመሆን በሀገር ውስጥ አቅም ሀብት የማሰባሰብ ሞዴል መፍጠር ችሏል። መንግስት እና የግሉ ዘርፍ ለኢኒሼቲቩ ገንዘብ ፈሰስ አድርገዋል።

ሀገር በቀል ፋይናንስ፣ የማህበረሰብ ጉልበትና የአይነት ድጋፎች ተዳምረው በአነስተኛ በጀት ፈጠራ የታከለበት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ ማከናወን እንደሚቻል አሳይቷል።


ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አየር ንብረት ለውጥ ፈንድ(GCF)፣ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮግራምና ሌሎች አጋሮች ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የገንዘብ ድጋፍና የቴክኒክ ድጋፎችን አግኝታለች።

የተገኘው ዓለም አቀፍ ድጋፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲዎች የበለጠ እንዲተሳሰሩ አድርጓል።

አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦችን ከኢኮኖሚ ልማት፣ ስራ ፈጠራ፣ አረንጓዴ ቱሪዝም እና ዘላቂ ግብርና ጋር በማስተሳሰር ሁሉን አቀፍ እይታን መፍጠር ችሏል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለሀገሪቱ የደን ሽፋን መጨምርም ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን 17 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን አሁን ላይ ሽፋኑ 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

አረንጓዴ ዐሻራ ከ20 ዓመት በፊት ከአራት በመቶ በታች የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን መልሶ እንዲያንሰራራ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የተራቆቱ አካባቢዎችን በፍጥነት ተንከባክቦ ማዳንና ምርታማ በማድረግ፣ የተራቆተ መሬትን በእጽዋት የማልበስ ስራ ላይ ጉልህ አበርክቶ አለው።

አረንጓዴ ዐሻራ የደን ሽፋንን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የደኖች ብዝሃ ህይወት ዳግም እንዲያብብና የማይበገር የአየር ንብረት ለውጥ አቅም ግንባታ ላይ የድርሻውን ተወጥቷል።

በአረንጓዴ ዐሻራ ለደንና ለውበት ከሚተከሉት ችግኞች ባሻገር በጥምር ደን እርሻ ለፍራፍሬና መኖ የሚውሉ ምግቦች በብዛት በማምረት በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል።

አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ከመትከል ዘመቻ ያለፈ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል፣ ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥና ዓለም አቀፍ ትብብርን የመፍጠር ትልቅ ውጥን ያለው ኢኒሼቲቭ ነው።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የአየር ንብረት ግቦች እንዲሳኩ በፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ በማህበረሰብ ተሳትፎ፣ በፈጠራ መፍትሄዎችና ሁሉን አቀፍ ተግባራት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉም የሚያመላክት ተምሳሌታዊ ኢኒሼቲቭ ነው።

ዓለም በአየር ንብረት ስጋቶች ውስጥ እየኳተነች ባለችበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ልምድ የተስፋ ጮራ የሆነና አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል በተግባር አሳይቷል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በተፈጥሮ ላይ እየሰራች የቀጣይ ትውልዶች መጻኢ ጊዜን እየጠበቀች ነው። ይህ ተግባር ከሀገር አልፎ ድንበርን ተሻግሯል።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የደን ሽፋንን ለመጨመርና የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያሉትን ተግባራት በተሞክሮነት ታጋራለች።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.