የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ሚና አሳድጓል - የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

Jul 23, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከናወኑ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራዎች የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተሳትፎ መጨመሩን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የግሉን ዘርፍ ተዋናዮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን በማሳተፍ በዘላቂ ልማት፣ በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊና በንግድ ዙሪያ የሚመክር የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ የግል ዘርፍ መድረክ ተካሂዷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከሰባት ዓመት በፊት የነበረው የልማት ፖሊሲ የሀገር ውስጥና የውጭ ብድር ክምችትን በማብዛት ሀገሪቱን ለከፍተኛ የእዳ ጫና የዳረገ ነበር፡፡


ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ መንግስት ዘላቂ የፋይናንስ ስርዓት በመዘርጋት የውጭ እዳ ጫናን መቀነስ፣ ኢንቨስትመንትን መሳብ እና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መገንባት ችሏል ብለዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ማሻሻያው ባለፈው አንድ ዓመት ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች የሚቀይሩ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባከናወነችው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አስገዳጅ የቦንድ ግዥን በማስቀረት ባንኮች ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ብድር መስጠት እንዲችሉ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በፊስካል ፖሊሲ እና በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በዚህም የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተሳትፎ አሳድጓል ብለዋል፡፡

የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በመጀመሪያ ዓመት ትግበራው የግሉን ዘርፍ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል፡፡

የመንግስት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ድሃ ተኮር መስኮች ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመግለጽ፤ ባለሃብቶች መንግስት የፈጠረውን እድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ጉባኤውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትብብር ያዘጋጁት ሲሆን የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ ለአካታች ፋይናንስና ልማት የብድር አገልግሎት ማመቻቸት፣ የኢንቨስትመንት ከባቢ በኢትዮጵያ እና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.