የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ብሎም ብልጽግና ያላት ቁርጠኝነት ዘመን ተሻጋሪ ነው

Jul 22, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ብሎም ብልጽግና ያላት ቁርጠኝነት ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያዘጋጁት ሶስተኛው የአፍሪካ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።


የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጉባዔው ቀጣናዊ የንግድ ትስስርና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ያለመ ነው።

በአፍሪካ ሀገራት የሚደረግ ንግድና የኢንቨስትመንት በአህጉሪቱ ያለውን የኢንዱስትሪ እምቅ አቅም በመጠቀም፣ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በማስፋፋት ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

የገበያ ትስስርን በማጎልበትም ለአገራቱ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም አንስተዋል።



ጉባኤው በአፍሪካ ሀገራት መካከል ስትራቴጂክ አጋርነትንና ትብብርን ለማሳደግ፣ አዳዲስ የገበያና የፋይናንስ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ሲሆን የገበያ እድሎችን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።

በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ በሃይል ትስስርና በሌሎች ቀጣናዊ ትብብርን ለማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ ዕድሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ብሎም ብልጽግና ያላት ቁርጠኝነትም ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዲናስር ተርኪ በበኩላቸው፤ ጉባኤው የአፍሪካን የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማነቃቃት የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።


አፍሪካ ለኢኮኖሚያዊ እድገትና ለልማት ያላትን ምቹ እድሎች ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና የሚጫወት ጉባኤ መሆኑን አመልክተዋል።

የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ሰፊ የህዝብ ቁጥር፣ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች ጨምሮ ሌሎች እድሎችና ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ ወጪ እና ገቢ ንግድ መሳለጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡


ለአብነትም አፍሪካዊያን ለዓለም የሚያቀርቧቸውን እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ አበባ፣ ማዕድናት እና ሌሎችንም ወደ ዓለም ሀገራት በማድረስ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በጉባኤው ኢትዮጵያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ ማዕድን እና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም እና ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን በማስመልከት ገለጻ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

በጉባኤው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) እና ያስሚን ወሃብረቢ፣ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ስራ አስፈጻሚ አብዲናስር ተርኪ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.