የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የአምቦ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መጥቷል - ተገልጋዮች

Jul 11, 2025

IDOPRESS

አምቦ፤ ሐምሌ 03/2017(ኢዜአ)፦ የአምቦ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተጋልጋዮች ቀደም ባለው ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዘጋጃ ቤት የረጅም ጊዜ ምልልስ ያደርጉ እንደነበረ ገልጸው ይህ ደግሞ ጊዜና ገንዘባቸው ያለአግባብ እንዲባክን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ የሚፈልጉትን አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ ባርሲሳ ማዴሳ፣ የከተማው ማዘጋጃ ቤት በአሁኑ ወቅት ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱን ለማግኘት በመጡበት ቀን ጉዳያቸውን ጨርሰው መመለሳቸውን ተናግረው አገልግሎት አሰጣጡ በዚሁ መልኩ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማጠናቀቂያ ፍቃድ ለመውሰድ ወደ ማዘጋጃ ቤት መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ በርሲሳ፤ ጉዳያቸውን በአንድ ቀን መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ በቀለ ጉተማ በበኩላቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት አንድ ጉዳይ ለመጨረስ ብዙ ጊዜ መመላለስ ያስፈልግ እንደነበር ገልጸዋል።


እሳቸውም የመስሪያ ማሽን ፈቃድ እድሳት ፈልገው መምጣታቸውንና በመጡበት ቀን አገልግሎት አግኝተው በመመላሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሃጫሉ ባጫ በበኩሉ ወደ ማዘጋጃ ቤቱ የመጣው የቤት ግንባታ ፍቃድ ለማውጣት መሆኑን ገልጿል።


ጉዳዩን በሁለት ቀናት ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጾ ቀድሞ ይህን አገልግሎት ለማግኘት እስከ ሳምንት ድረስ መመላለስ ይጠይቅ ነበር ብሏል።

በዚሁ ወቅት ግን የማዘጋጃ ቤቱ ሰራተኞች በሰዓታቸው ገብተው በአግባቡ ተገልጋዮችን እያስተናገዱ መሆኑን መታዘቡንም ተናግሯል።


የአምቦ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰኚ ታሲሳ እንደገለጹት የከተማው ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን ፍላጎት እና ጥያቄ መሰራት በማድረግ በየጊዜው አገልግሎቱን እያሻሻለ ይገኛል።

ባለ ጉዳዮች አገልግሎት ለመግኘት ወደ ማዘጋጃ ቤቱ ሲመጡ ሳይጉላሉ ፈጣንና ጥራት ያለውን አገልግሎት እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ማዘጋጃ ቤቱ የክልሉ መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ሰኞ፣ ረቡዕ፣ ዓርብ በሳምንት ሶስት ቀን የባለ ጉዳዮች ቀን ተብሎ ሁሉም ሰራተኞች ተገልጋዮችን ያስተናግዳሉ ብለዋል።

በዚህም ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልጸው አሁንም ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ያሉ በመሆኑ በቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ተገልጋዩ ህብረተሰብም በተለዩ የአገልግሎት መስጫ ቀናት ወደ ማዘጋጃ ቤት በመምጣት አገልግሎት ማግኘት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.