አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ከራዕይ ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ ዓበይት ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልገው ነገሮች መካከል አየር፣ ውሃ፣ ምግብ እንዲሁም ኢነርጂ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ምግብን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት መቻልን በውስጡ የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ወደ ስራ ገብታ ውጤታማ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች በማስመዝገቧም 2ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ስብሰባን ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ መመረጧን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የምግብ ስርዓት ሽግግርን የሚያፋጥኑ የተለያዩ ብሔራዊ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝም አስታውቀዋል።
ለአብነትም የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ኢትዮጵያ ታምርት እንዲሁም የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ኢንሼቲቮችን ጠቅሰዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተተገበሩት የሌማት ትሩፋት የወተት፣ የእንቁላል፣ የስጋ፣ የዓሳና የማር ምርታማነት በመጨመር ዜጎች በንጥረ ነገር የበለፀገ ምግብ አቅርቦትና ተደራሽነትን ማሻሻል ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባዔን በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ጉባኤው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ሽፋን በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው የዛሬው መድረክም የዚህ አንድ አካል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ ወደ ትግበራ ገብታለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ውጤታማ ተግባራት ዘላቂ እንዲሆኑ የተለያዩ ስራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ ሌሎችም ውጤታማ እንዲሆኑ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ዘገባዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ተደራሽ በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬው መድረክም በኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት የሽግግር ጉዞ እውን እንዲሆን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025