የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኦሮሚያ ክልል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው

Jul 8, 2025

IDOPRESS

ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ) ፡-የኦሮሚያ ክልልን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር በመደገፍ ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በኢንቨስትመንት ዙሪያ የጀመረውን ስራ የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።


የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢድሪስ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት በጥናት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

የክልሉ መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን በተሻለ መልኩ በመምራት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ሰፊ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ስምምነቱም ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ውጤታማነት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ዛሬ የተደረሰው ስምምነትም የአመራሩን የማስፈፀም አቅም ለማጠናከር የሚያግዙ ስራዎችን ለመስራት፣ የፖሊሲ ቀረጻና የገበያ ትንተናን ለማከናወን ይረዳል ብለዋል።

በተለይም በክልሉ ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች በጋራ የሚከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።


በተጨማሪም ስምምነቱ የክልሉን ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እና የገበያ ትስስር ማጠናከር የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

በስምምነቱም የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅና የክልሉን ለኢንቨስትመንት ምቹነት ለአለም ለማሳየት በጋራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ የምርምር፣ የማማከርና የስልጠና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ኮከብ ደመቀ (ዶ/ር) እንዳሉት በጥናትና በምርምር ለኢንቨስትመንት እድገትና ውጤታማነት ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ዩኒቨርሲቲው ያለውን ሰፊ ​​ልምድ ተጠቅሞ የክልሉን የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማ የሚያደርግ ጥናትና ምርምር ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.