የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

Jul 7, 2025

IDOPRESS

አሶሳ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ኡራ ወረዳ በ74 ሚሊየን ብር የተገነባ የመስኖ መሰረተ ልማት ስራ አስጀመርዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም አርሶ አደሩ ከመደበኛ የግብርና ስራው በተጨማሪ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

አርሶ አደሩ የመስኖ መሰረተ ልማትን ተጠቅሞ በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋጥ እንዳለበት ጠቁመው እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ብቻ በክልሉ 11 የመስኖ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።


የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበክር ኸሊፋ በበኩላቸው ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው የፀንፀሎ መስኖ ፕሮጀክት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደር ከባህላዊ የመስኖ ስራ በማላቀቅ የመስኖ ስራውን በስፋት ለማከናወን ያግዘዋል ብለዋል።


የፀንፀሎ ቀበሌ የመስኖ ፕሮጀክት በአካባቢው የሚገኙ ሶስት ቀበሌዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ከ800 በላይ ነዋሪዎች በመስኖ ልማት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።


በመስኖ ፕሮጀክቱ ምረቃ መርሃግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን በመስኖ ፕሮጀክቱ አካባቢም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.