የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

አዲስ አበባ የብልጽግና ጉዞ የመሪነት ሚናዋን ለማጠናከር ወሳኝ ለሆነው የመንገድ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታለች- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

Jul 7, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የመሪነት ሚናዋን ለማጠናከር ወሳኝ ለሆነው የመንገድ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታለች ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማው የተገነቡ 21 ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ለማዘመን ከኮሪደር ልማት ስራዎች ባሻገር የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

መዲናዋ በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የመሪነት ሚናዋን ለማጠናከር ወሳኝ ለሆነው የመንገድ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝ አስታውቀዋል፡፡

በበጀት አመቱ ብቻ በመዲናዋ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንገድ እና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት 31 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸዉ 13 የመንገድ ፕሮጀክቶችንና 8 ድልድዮችን አጠቃላይ 21 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ በበጀት አመቱ ወደ 15ሺ 960 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ እና የቃሊቲ ቅሊንጦ የመንገድ ግንባታዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማሳለጥ የትራፊክ ፍሰቱን በማስተካከል በኩል ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ወሳኝ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አንስተዋል።


በቀጣይ ለእድገት ዋና መሰረት የሆነውን የመንገድ መሰረተ ልማት ለማስፋት የከተማ አስተዳደሩ የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከተባበርን በርካታ ስራዎች መስራት እንደምንችል ያሳዩ ናቸው ያሉት ከንቲባዋ፤ በቀጣይ ለሚሰሩ የልማት ስራዎች ሁሉም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሞዲን ረሻድ(ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በርካታ መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ብለዋል።


በ2017 በጀት ዓመት የአስፓልት ፣የኮብልስቶን ንጣፍ፣ የጠጠር መንገድ ፣የእግረኛ መንገድ፣ የድጋፍ ግንብ እና የማፋሰሻ ቦዮች ግንባታዎችን ጨምሮ 371 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ መሰረተ ልማት መገንባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.