ሐረር ፤ ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ)፡- በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር እያለሟቸው ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች የገቢ ምንጭ በመሆን ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በሐረሪ ክልል በዘርፉ ልማት የተሰማሩ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተተከለው ከ11 ሚሊየን የሚበልጥ ችግኝ አብዛኛው ለምግብነት የሚውል መሆኑን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ገልጿል።
በተለይ በአረንጓዴ አሻራ የተተከለው ችግኝ በአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ውጤት እንዲመጣ ከማስቻሉ ባለፈ የደን ሽፋን ላይም መሻሻል ማሳየቱም ተመልክቷል።
በክልሉ ኤረር ወረዳ የቂሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር መሀመድ አብዱላሂ ከዘርፉ ልማት ተጠቃሚዎች አንዱ ናቸው።
አርሶ አደሩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከአምስት ዓመት በፊት በአረንጓዴ አሻራ የተዘጋጀ ችግኝ ከአቅራቢያ በሚገኘው ችግኝ ጣቢያ በመውሰድ ሲያለሙ እንደቆዩ ተናግረዋል።
በዚህም ማንጎ፣ዘይቱን፣አቡካዶ፣ፓፓያና ሎሚ በማሳቸው በመትከል ስራውን እንደጀመሩ በመጥቀስ።
በአረንጓዴ አሻራ ከተከሏቸው ፍራፍሬዎች እያገኙት ያለው ምርት ከፍጆታቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ በዓመት ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚሰበስቡ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሐረር ከተማ "ቪላ" ቤት መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ፍራፍሬ መትከል ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን አዕዋፍ ስለሚመገቡት ከፈጣሪ ዘንድም ጽድቀትን ያመጣል በባንክ ቤት ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖርህ ያደርጋል ያሉት አርሶአደሩ፤ ዘወትር ይህንን ስራ የዕለት ተዕለት አድረገው መቀጠላቸውን ነው የገለጹት።
ችግኝ መትከል የቤተሰብ ኑሮን ከማሻሻልና የገቢ ምንጭን ከማሳደግ ባለፈ የአፈር መከላትን የሚከላከልና ንጹህ አየር እንድናገኝ የሚያስችል ነው፤ ሁሉም በየወቅቱ ችግኝ መትከልና መንከባከብ አለበት ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ በሚገኘው ችግኝ ጣቢያ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ወይኒቱ ታምራት ናቸው።
በችግኝ ጣቢያው የተለያየ ፍራፍሬና የደን ችግኝ አዘጋጅተው ለተከላ ዝግጁ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ችግኝ በብዛት እየተተከለም እየፀደቀም መሆኑንም አንስተዋል።
የቂሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ መሀመድ አብራሂም በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ስራ የለኝም ነበር፤ አሁን በችግኝ ጣቢያ ውስጥ ተቀጥሬ እየሰራሁ እራሴንና ቤተሰቤን እየጠቀምኩኝ እገኛለሁ ብለዋል።
በየዓመቱ የሚተከለው የፍራፍሬና ሌላም ችግኝ ውጤታማ በመሆን አካባቢውን አረንጓዴና ነፋሻማ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
በዘርፉ ልማት የተሰማሩ ነዋሪዎች ፤ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር እያለሟቸው ያሉት የፍራፍሬ ተክሎች የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ሀብት እያፈሩ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
በክልሉ ዘንድሮ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉና ለዚህም ዝግጅቱ መጠናቀቁን የገለጹት በክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አራርሶ አደም ናቸው።
የሚተከሉትም በተለይ ክልሉ የሚታወቅበት ፍራፍሬ ከተዘጋጀው ቸግኝ ውስጥ አብዛኛውን እንደሚሸፍን ጠቅሰው፤ ቀሪው ደግሞ የሐረር ቡና፣ የእንስሳት መኖና ለደን አገልግሎት የሚውሉ መሆኑን አመላክተዋል።
የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ11 ሚሊየን የሚበልጥ ችግኝ መተከሉንና ከዚህም አብዛኛው ለምግብነት የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በአረንጓዴ አሻራ የተተከለው ችግኝ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ከማጎልበቱ ባሻገር የደን ሽፋን ላይም መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025