አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 28/2017 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሀገራት የአህጉሪቷን በምግብ ራስን የመቻል ራዕይን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ገለጹ።
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዴፕ) የ10 ዓመት ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ መካሄድ ጀምሯል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በአፍሪካ ለምለም መሬት ላይ የተስፋ ዘር ተዘርቷል፤ ዘሩም ሙሉ ፍሬ እንዲሰጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በካዴፕ የትግበራ ጉዞ ውስጥ ከማፑቶ ድንጋጌ ተነስቶ ወደ ማላቦ አሁን ደግሞ የካምፓላ ድንጋጌ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
በአፍሪካ የግብርና ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ የታመነበት አዲሱ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር ከእ.አ.አ 2025 እስከ 2036 እንደሚተገበር ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሀገራት በግብርናው ዘርፍ የሚያስመሰግን ለውጥ ቢያመጡም የካዴፕን ግቦችን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
የበጀት እጥረት፣ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ማነስ፣ መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለሟላት እና ሌሎች ፈተናዎች የፕሮግራሙ ውጤታማነት ላይ ተጽእኖ እንዳሳደሩ ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
አፍሪካ መሬት ፣ ውሃ እና የቴክኒክ አቅሞች እያሏት በዓመት ከ50 እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ምግብ ከውጭ እንደሚያገቡ ጠቁመዋል።
ኮሚሽነር ቪላካቲ ይህን ያህል ከፍተኛ ወጪ ለምንድነው የምናወጣው? ብለን ራሳችንን በመጠየቅ ምርታማነታችንን ማሳደግ ላይ በትጋት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
አዲሱ የካዴፕ ስትራቴጂ በምግብ ስርዓት ውስጥ በማምረት፣ በማቀነባበር፣ በማሰራጨት እና በመጠቀም ያለውን ሁሉን አቀፍ ሂደት የመቀየር ግብ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ስትራቴጂውን በብሔራዊ እቅዶቻቸው በማካተት በሙሉ አቅም እና ቁርጠኝነት እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ለግብርናው ዘርፍ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ እና ሀብት በማሰባሰብ ለውጤታማነቱ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ካዴፕን በሙሉ አቅም ከተገብርን በአፍሪካ ላሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ይቻላል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።
የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ሳይታክቱ በመስራት እና ራስን ለለውጥ በማዘጋጀት ለአፍሪካ የተስፋ እና የብልጽግና ጮራ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ (አውዳ-ኔፓድ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ በበኩላቸው የአፍሪካ ሀገራት ለማሳደግ እና ለመለወጥ የግብርና አቅማቸውን በሚገባ መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025