የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ እንድንጠቀም እድልን ፈጥሮልናል- አርሶ አደሮች

May 6, 2025

IDOPRESS

ዱራሜ ፡ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፡- በከምባታ ዞን የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በአካባቢያቸው ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እድልን እንደፈጠረላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ጆሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደሳለኝ ሎዴቦ ለኢዜአ እንደገለፁት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእጃችን ያሉ ሀብቶችና ጸጋዎችን በአግባቡ አውቀን የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን እያስቻለን ነው።

ከዚህ ቀደም የወተት ላም የማርባት ልምዱ ቢኖራቸውም ውጤታማ እንዳልነበሩ አንስተው በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ የነበሯቸውን የወተት ላሞች በተሻሻሉ የወተት ዝርያዎች በመቀየር ወደ እርባታ ገብተው የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።


120 አርሶ አደር አባላት በወተት መንደር በመደራጀት በተቀናጀ መንገድ ወተት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

ሌላኛው አርሶ አደር ወርቁ ወልዴ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ አርሶ አደሩ ባለው የመሬት መጠን በርካታ ተግባራትን እንዲያከናውን እድልን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡


በመንደሩ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር በመደራጀት ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ ዶሮ በማርባት እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም እያገኙት ያለው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ልጆቻቸውን በተገቢው መንገድ ከማስተማር በተጨማሪ ራሳቸውን በቁጠባ በማጠናከር ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡


የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ እንደገለፁት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል የወተትና የዶሮ እንዲሁም የንብ መንደር በመፍጠር በርካታ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ ውስን መሬትን ለዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲውል የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግሯል፡፡

በዚህም መርሃ ግብሩ የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡


በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ አርሶ አደሮች በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ተሳታፊ በመሆን እያስመዘገቡት የሚገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው አክለዋል፡፡

በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ጆሬ ቀበሌ በአንድ መንደር የተደራጁ 120 አርሶ አደሮች ላይ እየታየ ያለውን ዓይነት ለውጥ ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.