የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያ እና ጣሊያን የግብርና ትብብር ስምምነት ለምርታማነት ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል

Jul 30, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ እና ጣሊያን የግብርና ትብብር ስምምነት ለምርታማነት ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በግብርናው ዘርፍ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የጣሊያን ግብርና እና ምግብ ሉዓላዊነት ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ሎሎ ብሪጅዳ ተፈራርመዋል።


ስምምነቱ ኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚጫወት ነው ተብሏል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ስምምነቱ፥ የቡና ዕሴት ሰንሰለትን ማሳለጥ፣ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የቡና አምራች አርሶ አደሮችን መደገፍ እና የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያተኮረ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጣሊያን ዘመናዊ ግብርናን በመተግበር ከፍተኛ ተሞክሮ እንዳላት የጠቀሱት የግብርና ሚኒስትሩ፥ ስምምነቱ የስልጠና እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማካተቱን ተናግረዋል።

ጣሊያን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በግብርናው ዘርፍ በአጋርነት ለመሥራት ይፋ ባደረገችው ዕቅድ መሰረት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን የመግባቢያ ስምምነት በቀዳሚነት መፈራረሟን አንስተዋል።

የጣሊያን ግብርና እና ምግብ ሉዓላዊነት ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ሎሎ ብሪጅዳ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በትብብር 2ኛውን የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤን በስኬት ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ስምምነቱ ለሁለቱ ሀገራት የግብርና ምርታማነት ዕድገት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.