የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ምርታማነታችንን ይበልጥ ለማሳደግ በግብርና ባለሙያዎች ታግዘን በትጋት እየሰራን ነው

Jul 25, 2025

IDOPRESS

ደሴ፤ሐምሌ 17/2017(ኢዜአ)፦የሰብል ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በግብርና ባለሙያዎች ታግዘውና ግብአት ተጠቅመው በትጋት እየሰሩ መሆኑን በደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ።

የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች በጃማ ወረዳ የስንዴ ዘር ልማትን በይፋ አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተሳተፉት የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ሸህ ሰይድ እንድሪስ እንዳሉት፤ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው በተሻሻለ አሰራር ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ ነው።


የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ቀድመው በማግኘታቸው ዛሬ በዘመቻ አንድ ሄክታር መሬታቸውን በዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

ሰብሉን ከአረም በማጽዳትና ከተባይ በመከላከል የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ሌላው አርሶ አደር እሸቱ ነጋ በበኩላቸው፥የመኸሩ ዝናብ ለሰብል ልማት ምቹ በመሆኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት በዘርፉ ባለሙያዎች ታግዘው ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


ተገቢውን ግብዓት ተጠቅመው አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን የስንዴ ዘር ልማት ዛሬ መጀመራቸውን አንስተዋል።

የተጀመረው የዘር ስራ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የጃማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ለወጠኝ ጠጋው ናቸው።

አርሶ አደሩ በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ወይዘሮ ሀና አለባቸው በበኩላቸው፥በዞኑ ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የታቀደውን የምርት እድገት ለማሳካት የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በማቅረብ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።


በ2017/2018 የምርት ዘመን በዞኑ በአጠቃላይ 432 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 15 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ገልጸዋል።

በዞኑ በስንዴ ልማት 222 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ ዛሬ በተጀመረው ዘርም ከአንድ ሺህ 700 ሄክታር የሚበልጥ መሬት መሸፈኑን ጠቅሰዋል።

ወደ ዞኑ ከገባው 530 ሺህ ኩንታል ውስጥ የአፈር ማዳበሪያ 475 ሺህ ኩንታል የሚሆነውን ማሰራጨት መቻሉን ጠቁመው፥ ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.