አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦የተርክዬ ባለሃብቶች በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
ስምንተኛው የዓለም ኢንዱስትሪ ትብብር ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በፎረሙ 30 የተርክዬ ባለሃብቶች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ባዛርም ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በፎረሙ መክፈቻ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያና ተርክዬ የረጅም ጊዜ የንግድና ኢንቨስትመንት ወዳጅነት አላቸው ብለዋል።
ይህን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት መቀየር በመቻሉ በርካታ የተርክዬ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ-ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ግማሽ ያህሉ ከተርክዬ የመጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ባለሃብቶቹ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ባላቸው ተሳትፎም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በአሁን ወቅት ከ260 በላይ የተርክዬ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ መኖራቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ ይህም የአገራቱን ጠንካራ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንኑ አቅም የበለጠ ለመጠቀም ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ መፍጠር መቻሉን ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ባለሃብቶች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያመጡ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህ ረገድ የተርክዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አዎንታዊ ሚና አላቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተርክዬ ኤምባሲ የንግድ አማካሪ ጣሀ ሳላር ኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምቹ መዳረሻ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
የተርክዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመታገዝ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
የአለም ኢንዱስትሪ ትብብር ፎረም ፕሬዚዳንት ዩኩ ቤንጊሱ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ተርክዬ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሰረተ ልማትና የሕግ ማዕቀፍ ማደራጀቷ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን እንደሚያስችላት ጠቅሰዋል።
ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው የቀረቡ የተርክዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ ዕድል መኖሩን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የባዛሩ ተሳታፊዎች መካከል በእብነበረድ ማምረት የተሰማሩት ሀሰን ካክማክ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሰፋፊ ግንባታዎችን እያከናወነች መሆኑን መመልከታቸውን አንስተዋል።
ይህም በዘርፉ የግብዓት አቅርቦት ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
በሽቶ ምርት የተሰማራችው ጉላይ ሚግርዳጊ በበኩሏ በአገሪቱ ያለው ምቹ ትራንስፖርት ምርቶችን በቀላሉ ለማጓጓዝ ያስችላል ብላለች።
በሎጂስቲክስ ዘርፍ የተሰማሩት ሴስጂን አታግሉ በመርከብና በአውሮፕላን የሚመጡ ምርቶችን ለደንበኞች ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025