የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የታገዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

Jul 24, 2025

IDOPRESS

አዳማ፤ሐምሌ 16/2017 (ኢዜአ)፦የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ተደራሽ ለማድረግ በምርምር የታገዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የጤፍ ምርት ከፍተኛ ተመራማሪ አብዲ ጁፋር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፥ ኢንስቲትዩቱ የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የተደገፈ ስራ እየሰራ ነው።

ኢኒስቲትዩቱ በጤፍ ላይ ምርምር ማድረግ ከጀመረ አንስቶ እንደየአካባቢው የአየር ጸባይ ሁኔታ የጤፍ ምርትን ለማስፋፋትና የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችሉ ወደ 60 የሚጠጉ የጤፍ ዝርያዎች በምርምር መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በቂ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢያዎች ከ40 በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የጤፍ ዘር መለቀቁን ገልጸው፥ በዝናብ አጠር አካባቢዎች ደግሞ 15 እንዲሁም ለደጋ የአየር ጸባይ ሁለት ዝርያ፣ለመስኖ ልማት ተስማሚ የሆነ ደግሞ አንድ የጤፍ ዝርያ መለቀቁን አስረድተዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከዝርያ ማሻሻል ስራ ጎን ለጎን የጤፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂና ኤክስቴንሽን አሰራሮችን ለመተግበር በምርምር የተደገፈ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በብሔራዊ የጤፍ ምርምር ፕሮግራም አማካኝነት በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችንና መፍትሔዎች ዙሪያ ግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሌሎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኦሮሚያ፣አማራና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፥ በተለይም በምርምር የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱና በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

የምርምር ስራውን የበለጠ ለማጠናከር ለተመራማሪዎች፣ ለቴክኒሺያኖችና ለረዳት የመስክ ተመራማሪዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጤፍ የስነ ምግብ ስርዓት የሚፈልገውን ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ሳይነካ በዓለም እንዲታወቅ ጭምር ግብ ተቀምጦ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው፥ በምርምር የወጡ የጤፍ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ቴክኖሎጂዎቹ ውጤት እንዲያመጡ በኤክስቴንሽን አገልግሎት የተደገፉ ስራዎችን ከማጠናከር ጀምሮ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.