የኢትዮጵያ የምግብ ትራንስፎርሜሽን ስርዓት በወሳኝ የለውጥ እጥፋት ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ እያደገ ያለ ወጣት የስራ ኃይል፣ የመንግስት ቁርጠኝነት፣ እየተስፋፋ ያለ መሰረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እድገት፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ዓለም አቀፍ አጋርነት ለስርዓተ ምግብ ዘላቂ ለውጥ ትልቅ የሚባሉ እድሎች ናቸው።
የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ተደራሽነት በሚፈለገው መልኩ አለማደግ፣ የድህረ ምርት ብክነት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የከባቢ አየር ጉዳቶችና የተቀናጀ አሰራር ክፍተት የምግብ ስርዓቱ እየገጠሙት ካሉ ፈተናዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ኢትዮጵያ መልካም እድሎችን የበለጠ ለመጠቀምና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ላይ ትገኛለች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የተገቡ ቃል ኪዳኖችን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂካዊ ያለቻቸውን ሰባት የትኩረት መስኮችን ለይታለች።
እ.አ.አ በ2024 የወጣው የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የስርዓተ ምግብ ሪፖርት እንደሚያመላክተው የመጀመሪያው የትኩረት መስክ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ነው።
የግብርና ምርታማነትን መጨመር፣ ድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ እና ብዝሃ የምርታማነት ስርዓቶችን መተግበር እንደ ግብ ተይዘዋል።
የምግብ ደህንነትን ማሻሻል፣ የአርሶ አደሮችን ገቢና የግብርና ምርቶች ሽያጭ እና ትርፋማነትን ማሳደግ የተጠቀመጡ ግቦች ናቸው።
ሁሉም ዜጋ በሁሉም ጊዜ በቂ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ነው።
ረሃብን ማጥፋትና ሁሉንም አይነት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ማስቀረት እንደ እቅድ ከተያዙት ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው።
የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብርን ማስፋት፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማዕከል ያደረገ የግብርና ስራ፣ በምግቦች ላይ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን መጨመር እና ለእናቶችና ህጻናት የሚያስፈልጉ የተመጣጠኑ ምግቦችን ተደራሽ ማድረግ የሚወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎች ናቸው።
የምግብ እጥረትና መቀንጨርን በተለይም ከህጻናትና ሴቶች ላይ መቀነስ ከስራዎቹ የሚጠበቅ ውጤት ነው።
ሶስተኛው ስትራቴጂ ድንገተኛ አደጋዎችና ተጋላጭነቶችን የሚቋቋም የምግብ ስርዓት መገንባት ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
የምግብ ስርዓቱ ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭትና ላልተጠበቁ የኢኮኖሚ ክስተቶች በየጊዜው ምላሽ መስጠት የሚችልበትን አቅም ማጠናከር በግብነት ተይዟል።
ውጤታማ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን መተግበር፣ በአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ፣ የዋስትና ማዕቀፎችን መደገፍና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት እንዲሁም ተጽእኖዎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም መገንባት የሚወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎች ናቸው።
በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት የሚያጋጥመውን የተመጣጠነና በቂ ምግብ አቅርቦት ፈተናን መቀነስ እንዲሁም የቤተሰቦችና ማህበረሰቦችን አይበገሬነት አቅም ማሳደግ የተቀመጡ የውጤት መለኪያዎች እንደሆኑ ሪፖርቱ ያመለክታል።
አራተኛው ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስክ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥና በምግብ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ፍትሃዊነትና አሳታፊነትን ማስፈን ነው።
ለወጣቶች፣ ለሴቶችና ለተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድሎችን በመፍጠር አቅማቸውን የማጎልበት ግብም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው።
የህብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ከገበያ ጋር ማስተሳሰር፣ እሴት መጨመርን ማበረታታትና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማልማት ስራ እንደሚከናወን በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍል፣ የስራ እድል ፈጠራና በምግብ ስርዓት ውስጥ ማህበራዊ አካታችነትን ማረጋገጥ ከሚጠበቁ ውጤቶች መካከል ይገኙበታል።
ዘላቂ የከባቢ አየር ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽን ማጠናከር አምስተኛው ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫ ነው።
ተፈጥሯዊ ሂደትን የተከተለና ከባቢ አየርን ወደሚጠብቅ የምግብ ስርዓት የመሸጋገር እቅድ ተይዟል።
የግብርና ስርዓቶችን ከስነ ምህዳር ጋር የሚያቀናጅ ሁሉን አቀፍ አካሄድ መከተል፣ ብዝሃ ህይወትን መጠበቅ፣ የመሬት መሸርሸርን መከላከል፣ መልሶ መጠቀምን ጨምሮ የተሟላ የምርት አመራረትና አጠቃቀም ሂደቶችን የተቀናጀ ማድረግ ቁልፍ ተግባራት ሆነው ተቀምጠዋል።
ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ ከግብርና ስራ የሚመነጨውን የበካይ ጋዞች መጠን መቀነስና ስነ ምህዳር ለሰዎች የሚሰጡትን ጥቅም ማሳደግ የስትራቴጂካዊ ግቡ የውጤት መለኪያዎች ናቸው።
የስርዓተ ምግብ አስተዳደርንና የተቋማት ቅንጅታዊ ትብብርን ማጠናከር ሌላኛው ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስክ ነው።
የፖሊሲ መሰናሰልን መፍጠር፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማጠናከርና ያልተማከለ የትግበራ አሰራርን እውን ማድረግም የተቀመጡ ግቦች ናቸው።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የጋራ ትብብር ማጠናከር፣ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያካተቱ የቅንጅት አሰራሮችን መፍጠርና መረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ቀረጻን ማሳደግ ማስፈጸሚያ ስልቶች ናቸው።
አሳታፊ የውሳኔ ሰጪነትና ውጤታማ የስርዓተ ምግብ ፖሊሲዎች ትግበራ የሚጠበቁ የመጨረሻ ውጤቶች እንደሆኑም በሪፖርት ሰነዱ ተመላክቷል።
የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን አቅምን መጠቀም የመጨረሻው የትኩረት መስክ ሲሆን መረጃን፣ የዲጂታል መሳሪያዎችና የኢኖቬሽን ስነ ምህዳሮችን በመጠቀም ስርዓተ ምግብን የማዘመን ግብ ተይዟል።
የዲጂታል ግብርና አሰራሮችን መደገፍ፣ ለምግብ ስርዓት ምርምር አስፈላጊውን ፋይናንስ ማቅረብና መንግስትና የግሉ ዘርፍ በምርምርና ልማት ላይ ያላቸውን ትብብር የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
የምግብ ስርዓትን አቅም መጨመር፣ የገበያ ተደራሽነት ማስፋትና መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ሰጪነት የሚጠበቁ ውጤቶች እንደሆኑም ተመላክቷል።
የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ ወጣቶችን ማብቃት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም መገንባት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ግጭትን መከላከልና ሰላም ግንባታ እንዲሁም ፋይናንስና ኢንቨስትመንት ማሰባሰብ ሌሎች በስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች ውስጥ የተካተቱ ስራዎች ናቸው።
የግብርና ሚኒስቴር እና የስርዓተ ምግብ ሴክሬታሪያት የስትራቴጂካዊ ስራዎቹ ዋና አስተባባሪ ተቋማት ሲሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ የሁለትዮሽ ለጋሾች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የአርሶ አደር ማህበራት አጋሮች ናቸው።
ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎቹ ትግበራ እ.አ.አ በ2025 የተጀመረ ሲሆን እ.አ.አ እስከ 2030 ይቆያል።
ለስትራቴጂካዊ ጉዳዮቹ ማስፈጸሚያ ከአምስት እስከ ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግና ይህንንም ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከጋሾች የሚሟላ መሆኑ የሪፖርቱ ሰነድ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች እ.አ.አ በ2030 የማይበገር፣ ሁሉን አቀፍ፣ እኩልነት የተረጋገጠበትና ዘላቂ የምግብ ስርዓት የመገንባት ግብ አካል ነው።
ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የሀገራትን ብሄራዊ የስርዓተ ምግብ የማጠናከሪያ ስራዎች ይገመግማል።
ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ስራዎችና ተሞክሮዎቿን ታቀርባለች።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025