የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በከተማዋ ለወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊ የስራ ዕድል የማመቻቸቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

Jul 21, 2025

IDOPRESS

ባሕርዳር፤ ሐምሌ 12/2017(ኢዜአ)፡- በከተማዋ ሰላምን በማፅናት ለወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊ የስራ ዕድል የማመቻቸቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ተናገሩ።

የከተማዋ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ በባሕርዳር ተካሂዷል።


ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመድረኩ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪው ቁልፍ ተግባር የከተማዋን ሰላም በማፅናት ለሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስራዎች አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል።

በዚህም የስራና ስልጠና መምሪያን ጨምሮ የሌሎችም ተቋማት እቅዶች የሚሳኩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ሊከናወን የታቀደውን የስራ ዕድል ፈጠራ በላቀ ሁኔታ በመፈፀም ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በከተማዋ ሰላምን በማፅናት ለወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዘና ፍትሃዊ የሆነ የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ባሕር ዳር የክልሉ ሕዝብ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ወደ ከተማዋ የሚገባውን ስራ ፈላጊ ወጣት ታሳቢ ያደረገ የስራ ዕድል ፈጠራ አጠናክሮ በማስቀጠል ተኪና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በራስ አቅም በስፋት እንዲመረቱ የሚደረግ መሆኑን አንስተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመነ አሰፋ ፤ ባለፈው የበጀት ዓመት ለ48 ሺህ 790 ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 69 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ክንውኑ ከዕቅድ በላይ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የብድርና የመሬት አቅርቦትን በወቅቱ በማመቻቸት አመርቂና ለቀጣይ ስራ ተሞክሮ የሚወሰድበት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል።

የስራ ዕድል ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከል የከተማ ግብርና፣ ግንባታና አገልግሎት እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ በቀጣይ የስራ እድል የማመቻቸቱ ተግባር በስፋትና በፍትሃዊነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ ክህሎት መር የስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ሀብት በማፍራት እራስን ከመጥቀም ባለፈ ተኪና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማምረት የሚችል ሀይል መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክተው፤ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፍትሃዊና ግንባር ቀደም የስራ ዕድል ፈጠራ ማከናወኑን አንስተዋል።

በቀጣይም ይሄው አበረታች ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

እንደክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፍትሃዊና ወጣቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በመድረኩ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.