የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኮርፖሬሽኑ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ገንቢ ሚና እየተወጣ ነው

Jul 18, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግብዓት እና ማሽነሪዎችን አቅርቦት በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ገንቢ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከቻይና ዓለም አቀፍ ሲኖትራክ ኩባንያ ጋር የጭነት ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት ወኪል አቅራቢ መሆን የሚችልበትን ስምምነት ይፋ አድርጓል።


የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክፍሌ ወልደማርያም በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ የዓለም አቀፉን የሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ውክልና ነው።

ይህም በሁለቱ የልማት ድርጅቶች መካከል ያለውን አጋርነት በማሳደግ የንግድ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

ስምምነቱ በሁለቱ የልማት ድርጅቶች መካከል ላለው የጋራ ራዕይና መተማመን ማሳያ ነው ብለዋል።

ግብርና የአብዛኛው ህዝብ የኑሮ መሰረትና ለኢኮኖሚው ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የዘርፉን እምቅ አቅምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን፤ ውጤታማ የሎጂስቲክና አገልግሎት ሰንሰለት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ግብዓቶችን በማቅረብ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በግብርና እና በትራንስፖርት ዘርፍ እያስመዘገበች ላለው ተጨባጭ ለውጥ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በመሆኑም የሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች የአፈር ማዳበሪያን፣ ምርጥ ዘር፣ የግብርና ማሽነሪዎችን እና ሌሎች ግብዓቶችን በፍጥነትና በጥራት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የጎላ አበርክቶ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።


የሲኖትራክ ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት ዛዮ ሁዋ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት በቀጣናው ሰፊና ምቹ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በአጋርነት ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል።

የሲኖትራክ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በዓለም ዙሪያ በርካታ አጋር ድርጅቶች እንዳሉት በመግለጽ፤ ለኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በርካታ ተሽከርካሪዎች እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

ለዚህ የሚመጥን የመለዋወጫ እና ሌሎች አገልግሎቶችን በስፋት እንደሚያቀርቡ በመጥቀስ ትብብራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ግቦችን በማሳካት ለግብርና ምርትና ምርታማነት ገንቢ አስተዋጽኦ ከማበርከት ባለፈም መልካም ትብብርም ይፈጥራል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር የቤልት ኤንዴ ሮድ ኢኒሼቲቭን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.