የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም ለማድረግ ታዳጊዎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀት መቅረጽ ያስፈልጋል - ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር)

Jul 14, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም እንድትሆን ታዳጊዎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀት መቅረጽ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ገለፁ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች 4ኛውን የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና በሳይንስ ሙዚየም አስጀምሯል።


የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ለማብቃት በክረምት ስልጠና እንዲሁም ከትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር እውቀትና ችሎታ እንዲያዳብሩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሀገራት ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ቁልፍ መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

በኢትዮጵያም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም በሁሉም መስክ ቀዳሚ ለመሆን ታዳጊዎች ላይ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዘርፉ መሰረታዊ እውቀት ኖሯቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ስራዎች መካከል በዘርፉ የሰው ሃይል ማጎልበትና ግንዛቤ መፍጠር አንዱ መሆኑን ገልፀው 4ኛ ዓመቱን የያዘው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የክረምት ስልጠናም ተጠቃሽ እንደሆነ አንስተዋል።

የስልጠና መርሃ ግብሩ ከ3 ዓመት በፊት በ15 ተማሪዎች እንደተጀመረ ገልፀው አሁን ላይ በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በ4ኛው ዙር የክረምት ስልጠናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡ 3ሺህ ታዳጊዎች መካከል 300ዎቹ መስፈርቱን አሟልተው ወደ ስልጠና መግባታቸውን ገልጸዋል።

ስልጠናው ለሁለት ወራት የሚሰጥ ሲሆን፥ ታዳጊዎቹ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረታውያን፣ ሮቦቲክስ፣ ፕሮግራሚንግና ሌሎች ትምህርቶችን እንደሚወስዱም ተናግረዋል።

ከቴክኒካል ስልጠና ባሻገር ችግር ፈቺ፣ የቡድን ስራ፣ የስራ ፈጠራና የተግባቦት እና መሰል የህይወት ክህሎቶችን ማዳበር የሚያስችሏቸውን ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.