የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የተተገበረው ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲ ወጣቶች በእውቀታቸው ሥራ በመፍጠር ሀገር እንዲገነቡ እያስቻለ ነው - አቶ አደም ፋራህ

Jul 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ለውጡ የተገበርነው ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲ ወጣቶች በእውቀታቸው ሥራ እንዲፈጥሩና ሀገር እንዲገነቡ አቅማቸውን እያሳደገ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሔድ የቆየው የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም ተጠናቋል።


በመድረኩ የተገኙት አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገሮች በልማት በሚተሳሰሩባቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።

ከእነዚህም ውስጥ የአህጉሪቱ ወጣቶች በልማት፣ በኢኮኖሚና በስራ እድል ፈጠራ የሚቀናጁበትን ሁኔታ ማመቻቸት አንዱና ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም እምቅ የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በለውጡ ዓመታት ብዝሃ ኢኮኖሚ እና አካታች ልማትን ከክህሎት መር የሥራ ፈጠራ፣ የትምህርትና የስልጠና ፖሊሲ ጋር በማስተሳሰር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበችበት ነው ብለዋል።

በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ልማት፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ኢኮኖሚ ተከታታይ ፈጣን እድገትና በርካታ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የሰው ሀብት ልማት የሰጠችው ትኩረት በእውቀታቸው ሥራ የሚፈጥሩ እና ሀገርን የሚገነቡ ወጣቶችን ማፍራት እያስቻለ ነው ብለዋል።

የአህጉሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ አካታች የኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሀገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።


የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

አማራጭ የሥራ እድሎችን የማስፋት፣ በየዘርፉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የማስረፅና ወጣቱ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተሳትፎ ማጉላት ላይ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል።

የአፍሪካ ሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም የአህጉሪቱ ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።

ፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት በቀጣይ በዘርፉ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ከማድረግ ባለፈ ቀጣይ በንግድና ሥራ ፈጠራ ላይ አበክረው ለመስራት አቅጣጫዎችን ያስቀመጡበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.