የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በመተግበር መሪ ሚናዋን እየተወጣች ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

Jul 8, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ አካታች ልማት እና ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በመተግበር መሪ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

በአህጉሪቱ ሁሉን አቀፍ ብልፅግና እና ዘመኑን የዋጀ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል የጋራ ሥራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሦስተኛው የአፍሪካ ሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።


የወጣቶች አህጉር የሆነቺው አፍሪካ እያደገች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወጣቶች የዕድገት ኃይሎቿና የነገ ተስፋዎቿ ናቸው ብለዋል።

የፓንአፍሪካኒዝም አቀንቃኟ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የመሪነት ሚናዋን በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና እና በፓን አፍሪካዊ የስራ ፈጠራ ለመድገም ጽኑ አቋም ይዛ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ግብይትን፣ የኢንዱስትሪ መነቃቃትን፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥር በመሆኑ ኢትዮጵያ ለተግባራዊነቱ እየተጋች ነው ብለዋል።

ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገትና መሰል ፈጣን ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እያስተናገደች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ይህን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሀገራዊ ሪፎርም ላይ መሆኗን አስገንዘበዋል።


በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ተጨባጭ የሰው ኃይል ግንባታ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንደምትገኝም አረጋግጠዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሀገራዊ አቅም እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና በማዘመን የአርሶ አደሩ ምርታማነት እየጨመረ ነው ብለዋል።

ኢንዱስትሪን በማስፋፋትም አርሶአደሩ ለምርቶች እሴት እየጨመረ ለገበያ እንዲያቀርብ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለበርካታ ዜጎች በገጠርና በከተማ የሥራ ዕድል በመፍጠር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መፋጠኑን አንስተዋል።

በዚህ ዘመን ሰውሰራሽ አስተውሎትና ፈጠራ ነባሩን የሥራ አውድ እየቀየሩት መሆኑን በማንሳት ከዚህ አኳያ አፍሪካውያን ዘመኑን የዋጀ ዝግጅት ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ወጣቶቿ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ብርቱ ሥራዎችን እየተገበረች መሆኗንም ገልጸዋል።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታም አካታችነትን በማረጋገጥ በገጠር ጭምር አነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጣሪዎችን እያፈራች ነው ብለዋል።


አፍሪካ መንገዶች እና ድልድዮችን ብቻ ሳይሆን አስተሳሳሪ፣ አካታችና ኢኮኖሚን የሚያነቃቁ ዲጂታል መሰረተ ልማቶች እንደሚያስፈልጓት በመጥቀስ፥ ለዚህ ደግሞ ብቁ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በክህሎት መር እሳቤዋ የላቀ የሰው ኃይል እየገነባች እንደምትገኝም አስረድተዋል።

የአፍሪካ ሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በፓን አፍሪካዊ እሳቤ አካታች ልማትን፣ ዘላቂና ምቹ የሥራ ዕድልን በመፍጠር የተሻለች አህጉር ለመገንባት ለተግባር በአንድነት የምንነሳበት ነው ብለዋል።

በፎረሙ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ አሊ የሱፍ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የዘርፉ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.