ሚዛን አማን፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጀት ዓመቱ ከ56 ሺህ ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለጸ።
አርሶ አደሮች በበኩላቸው ገበያን መሰረት አድርገው ከሚያለሙት የቅመማ ቅመም ምርት የተሻለ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ በረከት እዮብ እንደገለጹት በክልሉ የሚመረቱ የቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
ክልሉ ለቅመማ ቅመም ያለውን ምቹ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ለውጭ ገበያ ቀርበው ምንዛሬ የሚያስገኙ ቅመማ ቅመሞችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት መደረጉንም አመልክተዋል።
በክልሉ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ቅመማ ቅመም መልማቱን የገለጹት ወይዘሮ በረከት በበጀት ዓመቱም ከ56 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።
የሸካ ዞን ግብርና፣ ደን አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳለኝ በዞኑ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች በስፋት እንደሚመረቱ ገልጸዋል።
ለአብነትም በዞኑ የኪ ወረዳ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርድ እንደሚያመርቱ ተናግረዋል።
እርድ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ዝንጅብልና ኮሮሪማ በዞኑ በዋናነት ከሚመረቱ የቅመማ ቅመም አይነቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸው፣ በዓመት ከ15 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለገበያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በወረዳው የኅብረት ፍሬ ቀበሌ አርሶ አደር ሁሴን ድርብ የእርድ ቅመም ልማት ቋሚ የመተዳደሪያ ገቢ የሚያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
ካላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት የእርድ ማሳ በማምረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
አምና ከ10 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰው ዘንድሮ ለእርድ ልማት ሥራ በሰጡት ትኩረትና እንክብካቤ ከእስካሁኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
ሌላው አርሶ አደር ይመር እሸቱ በበኩላቸው ከዓመት ወደ ዓመት የእርድ ምርት ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ማሳቸውን አስፋፍተው በማምረታቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የገበያ ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በኩታገጠም የእርሻ ዘዴ በማልማት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025