የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ከተማ አስተዳደሩ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማት ስራዎችን አከናውኗል

Jul 4, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ደህንነቱን ውጤታማ በማድረግ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማከናወኑን በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ( ኢ/ር) ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አመታዊ ጉባኤ ተካሄዷል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አስራ አምስት የከተማ አስተዳደሩ ተቋማትን የያዘ በከተማው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የጋራ ተልዕኮ የወሰደ ነው።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ እና የመንገድ ደህንነት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ደህንነት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።


አስተዳደሩ የመንገድ ደህንነትን ውጤታማ በማድረግ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማከናወኑን አስታውቀዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ምቹና ዘመናዊ የእግረኛ መንገድ መገንባታቸው እንዲሁም አስፓልቶች ዘመናዊ ፓርኪንጎች ሌሎች በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

መሰረተ ልማቶችና ሌሎች ስራዎች የመንገድ ደህንነትን በማረጋገጥ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

አሁንም በከተማዋ የትራፊክ አደጋ የሚያልፈውን የሰው ህይወት እና የንብረት ውድመት ለመቀነስ ሁሉም በአግባቡ ሀላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ እና የመንገድ ደህንነት ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ያብባል አዲስ በበኩላቸው፤ የከተማዋ አስተዳደር የመንገድ ስትራቴጂ ከማውጣት በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማትን በአዲስ አደረጃጀት በማቋቋም እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡


በተሰራው ስራም ለውጦች ቢኖሩም የትራፊክ አደጋ አሁንም በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ችግሮች ማድረሱ እንደቀጠለ መሆኑን አንስተው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ትልቅ ስራ መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ምክር ቤቱ የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንጻር በቅንጅት የሚሰራውን ስራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እና የመንገድ ደህንነት ምክር ቤቱ ጸሀፊ ክበበው ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ የጋራ ተልዕኮዎችን በመፈጸም አበረታች ስራዎች መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በበጀት አመቱ የግንዛቤ ስራ፡ የቁጥጥር ስራ እንዲሁም ህግ በሚተላለፉ ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀው በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡


በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አመታዊ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.