አዳማ፤ ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተደረገ ያለው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ ኤሊያስ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩን በስኬት ለማከናወን ከችግኝ ዘር አቅርቦት ጀምሮ ስብጥሩን በጠበቀ መልኩ እየተሰናዳ ነው።
በዚህም በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያግዙና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ሀገር በቀል ዛፎች፣ ፍራፍሬና የእንስሳት መኖ ችግኝ ትኩረት እንደተደረገባቸው ጠቅሰዋል።
በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተዘጋጀው ችግኝ ውስጥ 11 በመቶ ለምግብነት የሚያገለግል አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ዘይቱን፣ ቴምርና ማንጎን ጨምሮ በፍጥነት ምርት የሚሰጡ የተለያዩ ዝርያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቀሪው ለደን ልማትና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላውን ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለማከናወን ታቅዶ የተከላ ቦታ ልየታና የጉድጓድ ዝግጅት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት።
የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰይፈዲን መሃዲ በበኩላቸው፤ በችግኝ ጣቢያዎች የሚዘጋጀው ችግኝ ያለበትን ሁኔታ በየጊዜው በመስክ እየገመገሙ ለተከላ መድረሱን እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀገር በቀል ዛፎች ዝሪያን ለመጠበቅ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ዝግጅት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በተለይ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን እውን ለማድረግና የደን ሽፋኑን በአስተማማኝ ለማሳደግ የሀገር በቀል ዛፎች ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ የደጋ ፍራፍሬ በተለይ የአፕል ችግኝ በስፋት መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
የክልሉን የደን ሽፋን ለማሳደግ ግብ መቀመጡን ጠቁመው፤ ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ተከላ የሚጀመርበት ወቅት እየተቃረበ በመሆኑ የጉድጓድና ሌሎች ተጓዳኝ ዝግጅቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025