ደብረማርቆስ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፡- በደብረ ማርቆስ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ተመስገን ተድላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የከተማውን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም ዘርፉን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ለ150 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ39 ባለሀብቶች ፈቃድ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶቹ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገበ በኢንዱስትሪዎች፣ በአገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች ለመሰማራት መሆኑን አስታውቀዋል።
ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ ስድስቱ ግንባታ የጀመሩ፤ ስምንቱ ቅድመ ግንባታ ዝግጅት ላይ እንዳሉ ጠቅሰው፤ ቀሪዎች ወደ ግንባታ ለመግባት በሂደት ላይ እንዳሉ አስረድተዋል።
ባለሀብቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ከ2ሺህ 500 ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ሌላ በከተማ አስተዳደሩ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ መንደር ገብተው እያለሙ መሆናቸው ጠቁመዋል።
ከ4ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ሲሉም የመምሪያው ሃላፊ ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህ ደግሞ ባለሃብቱ እንደተግዳሮት የሚያነሳቸውን የመሠረተ ልማት ችግር ለመፈታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነት ከተማ አስተዳደሩ እና የክልሉ መንግስት የኤሌክትሪክ ሃይል ማነስና መቆራረጥ ችግር ለማቃለል ከ38 ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ ወደ ተግባር የተገባውን ጠቅሰዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል አቶ አዲሱ ካሴ በሰጡት አስተያየት፤ የሶፍት ፋብሪካ ለመገንባት ከ2ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ተሰጥቶኝ ወደ ግንባታ ገብቻለሁ ብለዋል።
በሁለት ዓመት ውስጥ አጠናቀው ወደ ስራ ለመግባት ማቀዳቸውን ጠቁመው፥ በዚህም ከ50 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።
የፕላስቲክ ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ፈቃድ የወሰዱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ሆድሞኝ የሻነው ናቸው።
በከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስጄ በተሰጠኝ ቦታ ለግንባታ ቅድመ ዝግጅት እያደረግኩ ነው ብለዋል።
ለፋብሪካው ማቋቋሚያ ከ1መቶ ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል እንደተያዘለትም ጠቁመው፤ ፋብሪካው ወደ ማምረት ሲገባ እስከ 70 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም አስታውቀዋል።
በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት 69 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውም ተጠቁሟል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ በልዩ ትኩረት መረባረብ እንደሚገባ...
Feb 28, 2025
ሐረር፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፦የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር በነበረበት የሚቀጥል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስ...
Feb 8, 2025