የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>በሀረሪ ክልል በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሳተፉ ሴት አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው እያደገ ነው</p>

Jan 18, 2025

IDOPRESS

ሐረር፤ ጥር 9/2017(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሳተፉ ሴት አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ተናገሩ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ለሞዴል ስምንት ሴት አርሶ አደሮች 350 ሺህ ብር ግምት ያለው የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችና የፀረ ተባይ ኬሚካል መርጫ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ለሞዴል ሴት አርሶ አደሮቹ ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው በከተማ ግብርና እና በገጠር ወረዳ በመስኖ ልማት ተሰማርተው ውጤታማ ለሆኑ ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች ነው።


አርሶ አደሮቹ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመሳተፍ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት በግብርናው ዘርፍ በክልሉ እየተመዘገበ ለሚገኘው አበረታች ውጤት የበኩላቸውን በማበርከታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሴቶችን በግብርናው ዘርፍ ማሰማራት ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የስራ እድል ፈጠራን ማስፋት እንደሆነም አክለዋል።

ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በግብዓትና ቁሳቁስ አቅርቦት ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በከተማው አባድር ወረዳ በከተማ ግብርና የተሰማሩት ወይዘሮ ሩሚያ አህመድ በበኩላቸው ከቢሮው ያገኙት የውሃ መሳቢያ ፓምፕም ድጋፍ ለስራቸው ስኬት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በአካባቢ የሚገኙ ወንዞችን በመጠቀም በበጋ ወራቱ የጀመሩትን የመስኖ ልማት ስራን ለማጎልበት ድጋፉ ምቹ አጋጣሚ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኤረር ወረዳ ሴት አርሶ አደር በቱላ መሀመድ ናቸው።

የሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ የበጋ መስኖ ልማት ስራን ውጤታማ ለማድረግ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ምርጥ ዘር እና የግብርና ልማት መሳሪያዎችን ባለፈው ወር ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.