አዲስ አበባ፤ሐምሌ 23/2017(ኢዜአ)፦ብሔራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታ ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከ2025 እስከ 2030 ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ብሔራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርገዋል።
ብሔራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታው በግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ ተሳትፎን በማሻሻል ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ብሎም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሏል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ፍኖተ ካርታው ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ለአርሶና አርብቶ አደሩም ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።
ፍኖተ ካርታው የፋይናንስ ተቋማትን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ ተደራሽነት የሚያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ ለሀገር የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የግብርና ፋይናንስ ፍኖተ ካርታ ለግብርናው ዘርፍ ታሪካዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ የግብርናውን ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ግብርና ሚኒስቴር ከ10 ሚሊዮን በላይ የአርሶ አደሮችን መሬት መመዝገቡን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ደግሞ የአርሶ አደሮችን እንስሳት የመመዝገብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ይህን መረጃ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶ አደሩ ያለ ማስያዣ የመሬት መጠቀሚያ መብቱን እና እንስሳቱን በማሳያዝ ብድር የሚገኝበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማትም ከፋይናንስ አቅራቢነት ባሻገር በሁሉን አቀፍ ዕድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ የሚያስቀምጡበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፤ ፍኖተ ካርታው የፋይናንስ ተቋማት የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ፍኖተ ካርታው ለአርሶ አደሮች የተሳለጠ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማደረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ ያሉ ተዋናዮች ሁሉን አቀፍ፣ የበለፀገ እና ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ምቹ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡት የኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደርቤ አስፋው፤ ባንኮች ለፍኖተ ካርታው ውጤታማነት የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ፍኖታ ካርታው ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት በማሳተፍ ምርታማነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ የፋይናንሻል አገልግሎት ግሩፕ ዳይሬክተር በበኩላቸው ፍኖተ ካርታው የአርሶ አደሩን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ከመሠረቱ የሚፈታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025