የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በከተማው የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

Jul 30, 2025

IDOPRESS

ጉደር፤ ሐምሌ 22/2017(ኢዜአ)፦በጉደር ከተማ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ገለጸ።

የጉደር ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሚልኬሳ ደንደና ለኢዜአ እንደገለጹት፥በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የህዝቡን የልማት ጥያቄ የሚመልሱ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ናቸው።

ለአብነትም አዲሱን ማስተር ፕላን ተከትለው እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከተማዋን ውብና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም ፈጥረዋል ብለዋል ፡፡


ከግንባታዎቹ መካከልም የመንገድ ዳር ማስዋብ፣ የአደባባዮች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችና የመዝናኛ ስፍራዎችን ያቀፈው የኮሪደር ልማት ስራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮሪደርና ሌሎች በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያሳድገዋል ብለዋል።

የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ያለመ ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ ከአምቦ ከተማ የውሃ ቦርድ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽት ለማስፋትም በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መገንባቱን አንስተዋል።

በከተማዋ ከሚከናወኑት የ4 ኪሎ ሜትር አዲስና ነባር መንገዶች ግንባታ መካከል 2 ኪሎ ሜትሩ የውስጥ ለውስጥ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከተማዋን ከገጠር ቀበሌዎች ጋር የሚያተሳስር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የጉደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በቀለ ጋቢሳ በበኩላቸው፤ በከተማው አስተዳደር እና በሕብረተሰቡ ተሳትፎ እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ በመሆናቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በተለይም የኮሪደር ልማቱ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና ከተማዋን ለቱሪስት ምቹ ለማድረግ በማገዙ ተግባሩን በመደገፍ በፍጥነት ለአገልግሎት እንዲበቃ እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ አለማየሁ ደንደና በበኩላቸው ከተማዋ ከኮሪደር ልማቱ በፊት አብዛኛው የንግድ ቤቶች በፕላስቲክ መሸፈናቸው የከተማዋን ውበት ከመቀነሳቸው ባለፈ በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ችግር መፍጠራቸውን ተናግረዋል ።


የኮሪደር ልማቱ ጠባብ የነበሩ መንገዶችን በማስፋት የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግና ለወጣቶች አማራጭ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.