ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 18/2017 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ክህሎታቸውን በማጎልበት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በአማራ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ስልጣኞች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዜጎች በዌብ ፕሮግራሚንግ ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ ፣ዳታ ሳይንስና አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የኢትጵያዊያን ኮደረስ ስልጠና በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ወጣቶች አቅማቸውን ለማሳደግና ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን ስልጠናውን “ በኦን ላይን” ሲከታተሉ ቆይተዋል፤ ስልጠናው አሁንም ቀጥሏል።
ስልጠናው ከቀጠለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የአማራ ክልል ይገኝበታል።
በአማራ ክልል 187 ሺህ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደው በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸው ተመልክቷል።
ስልጠናውን ከተከታተሉ ሰልጣኞች መካከል በክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለሙያ አዲሱ ፅጌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት እድል ያመቻቸ ነው።
የዓለም የስራ ባህል በቴክኖሎጂ ምክንያት እየተቀየረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህን የሚመጥን እውቀትና ክህሎት በማዳበር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ስልጠናው ወሳኝ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ በሀገሪቱ የተጀመረው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ስራዎችን ከዘመኑ ጋር አስተሳስሮ ለማከናወን የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ከዘመኑ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ለመጓዝ በአጫጫር ስልጠናዎች ራስን ማብቃት የግድ እንደሆነም ተናግረዋል።
በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መሳተፍም የቴክኖሎጂ ክህሎትን እንዳሳደገላቸውና በዓለም ዓቀፍ የስራ ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ እያገዛቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
ሌላው የዚሁ ተቋም ሰልጣኝ ይበልጣል ዓለሙ እንደገለጸው፤ ስልጠናው መንግስት ለቴክኖሎጂ እድገት የሰጠውን ትኩረት በተግባር ያረጋገጠ ነው።
በስልጠናው የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎቱን በማሳደግ ለተቋሙ ስራን የሚያሳልጡ ሶፍት ዌር ማበልፀጉን ተናግረዋል።
ስልጠናውም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደጉ ሁሉም ሰው በተነሳሽነት እንዲወስደው አስተያየት ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሸቲቭ የቴክኒካል ኮሚቴ አባል አቶ አማረ ዓለሙ፤በክልሉ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 760 ሺህ ዜጎችን ለማሰልጠን ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም 191 ሺህ 992 ዜጎችን በስልጠናው ለማሳተፍ ታቅዶ 187 ሺህ ዜጎች መሰልጠናቸውን አስታውቀዋል።
ስልጠናውን ወስደው ካጠናቀቁት መካከልም 65 ሺህ የሚሆኑት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ሌሎች የስልጠና ማዕከላት ባለሙያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ዕቅዱን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ኢኒሼቲቩ በተቀናጀ መንገድ እንደሚተገበር አንስተዋል።
አሁን ላይ በስልጠናው ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ቁጥር በእጅጉ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025