የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የእርሻ መሬትን ደጋግሞ በማረስ እና በኖራ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራን ነው-የጌዴኦ ዞን አርሶ አደሮች

Jul 25, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ ሐምሌ 17/ 2017 (ኢዜአ)፦ለመኸር እርሻ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ እና አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ በተያዘው የመኸር እርሻ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን የማሳ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁ ተመላክቷል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አርሶ አደሮች መካከል የቡሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ አማኑኤል ተፈራ እንደገለጹት በመኸር እርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ ቀደም ብለው የማሳ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።


በአቅራቢያቸው ካሉ አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም ለማልማት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ አሲዳማ መሬቶችን በኖራ ማከማቸውን ተናግረዋል።

የታከመ የእርሻ መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ ማለስለሳቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ፤ በአሁኑ ወቅት ገብስ፣ ባቄላና ድንች ለመዝራትና ለመትከል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ የማሳ እንክብካቤን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀድመው ማግኘታቸው ትኩረታቸውን የማሳ ዝግጅት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ እድል መስጠቱን የገለጹት ደግሞ በይርጋጨፌ ወረዳ የቱቲቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፀጋዬ ሮቤ ናቸው።


በኩታ ገጠም በ10 ሄክታር መሬታቸው ላይ ስንዴ ለመዝራት የዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀናት የዘር ሥራ በማከናወንና የእንክብካቤ ስራዎችን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ ተግተው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በጌዴኦ ዞን የቡሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ ሽፈራው በበኩላቸው እንዳሉት በወረዳው 4 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በዘር ለመሸፈን የእርሻ ዝግጅት ሥራ አጠናቀዋል።


ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ቀድሞ ከማድረስ በተጨማሪ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

አንድም መሬት ጾም እንዳያድር የተቋማትና የወል መሬቶች ጭምር እንዲለሙ መደረጉን ገልጸው፣ ሰፋፊ እርሻዎችም በክላስተር እየለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎‎በመኸር ወቅት ገብስ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ስንዴና ድንች ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ በድሉ አየለ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት ለግብርና ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

በተለይ በተያዘው የመኸር ወቅት የግብአት አጠቃቀምን በማሻሻልና አሲዳማ መሬቶችን በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በዞኑ የአሲዳማነት ችግር ያለባቸውን መሬቶች ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ተጠቅሞ በማከም ከምርት ውጭ የነበሩ መሬቶችን ወደልማት ለማስገባት ተችሏል ብለዋል።


የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ እንዲደርስ መደረጉን ጠቁመው፣ በዚህም በግብዐት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ችግር አለመግጠሙን ገልጸዋል።

በዞኑ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ወቅት በዘር ለመሸፈን የማሳ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ ወደዘር ሥራ እየተገባ መሆኑንም አቶ በድሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.