የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ43ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል በቡሳ ጎኖፋ ይለማል

Jul 25, 2025

IDOPRESS

ሐረር፤ ሐምሌ 17/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ43ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል በቡሳ ጎኖፋ እንደሚለማ የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ አስታወቀ።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በቡሳ ጎኖፋ የሚለማ የመኸር ሰብል በዘር የመሸፈን ሥራ በባቢሌ ወረዳ ተጀምሯል።


የቡሳ ጎኖፋ አሮሚያ ሃላፊ መሐመድ ጁንዳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት በትኩረት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የጋራ አቅምን በአግባቡ መጠቀም የሚቻልበት የቡሳ ጎኖፋ አንዱ ነው።

ቡሳ ጎኖፋ በቀዳሚነት የህዝቡን ነባር የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል በመጠቀም ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋ የተጋለጡ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ስራ የሚሰራበት ሥርዓት ነው።


ለዚህም የሰው ጉልበትንና መሬትን በመጠቀም በዘንድሮው የመኸር ሰብል ከ43ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡሳ ጎኖፋ ለማልማት ከታቀደው ውስጥ ከ20ሺህ በላይ መሬት በዘር የመሸፈን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በተለይም ሰፋፊ መሬት ባለባቸው አካባቢዎች ሰብልን በማልማት የአደጋ ግዜ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በምናከናውነው ስራ የቡሳ ጎኖፋ የእርሻ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት አሳይተዋል ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ ናቸው።


ህዝብን በማቀናጀት የሚከናወኑ ስራዎች ከራስ አልፎ ሌሎችን መደገፍ እንደሚያስችል የተመለከትንበት ስራ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ቡሳ ጎኖፋ የስራ ባህልን በማጠናከር ተረጂነትን በመቀነስ ራስ የመቻል ባህልን እያጎለበተ ነው ያሉት ደግሞ የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈዲላ ዳውድ ናቸው።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የእርሻ ስራ በህብረተሰቡ ዘንድ ተረጂነት እየተቀረፈና የይቻላል ስሜት እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመዋል።


ዘንድሮም በዞኑ 1ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሰብል የማምረት ስራ እንደሚከናወን በመግለጽ።

ቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችን እንዲጎለብት ማድረጉን የጠቀሱት በባቢሌ ወረዳ አርሶ አደር ዩስፍ አህመድ፤ ይህንን ምርታማነት የሚያጎለብትና መደጋገፍን የሚያጠናክር ተግባርን እናስቀጥላለን ብለዋል።


የኦሮሞ ህዝብ የመረዳዳት ባህል እና እሴት የሆነውን ቡሳ ጎኖፋን ከመንግስት ጎን በመሆን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ የተናገሩት ደግሞ የባቢሌ ወረዳ አርሶ አደር መሀመድ አብዲ ናቸው።


የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.