ወላጆቻችን ዘወትር ጠዋት ወደ ስራቸው ከመሰማራታቸው ወይም ከቁርስ በፊት “አማን አውለን፤ ውሏችንን አሳምርልን፤” ብለው ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ፡፡
ውሎ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡የሰውን ልጅ አካላዊ፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ እድገት ይወስናል፤ ማንነትንና አስተሳሰብን ይቀርፃል፡፡ይህ በበኩሉ የምንኖርበትን አውድ ይፈጥራል፡፡ አውዱ በጎም፣ መጥፎም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የሚወሰነው በተቀረጽክበት እሳቤ ነው፡፡
ይህን ጉዳይ በፖለቲካው አውድ ከፍ አድርገን ካየነው ተመሳሳይ ሁኔታን እናገኛለን፡፡ በፖለቲካዊ ሁኔታዎች ውስጥ የሰው ልጅ ባህሪ በምክንያታዊነት ወይም ግላዊ ሁኔታ ብቻ አይወሰንም። ይልቁንም በማህበራዊ ግንኙነትና እሱ በሚፈጥረው ካባቢያዊ አውድ መስተጋብር ጭምር ነው፡፡
“ጠብ መንጃ” አንጋቾችም ይሁኑ ቆሞ ቀር ፖለቲከኞች፣ ባንዳዎች እና አጫፋሪዎቻቸው ለምንድን ነው ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ከሌላው በተለየ ሁኔታ ነጥለው ማጥቃት የሚፈልጉት? የሚለውን ጥያቄ ካየን፣ ጉዳዩ ከውሎ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሎ አረንጓዴ አሻራ ለማኖር ጫካ ነው። የስንዴ፣ የሩዝ፣ የቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ነው። የኮሪደር ልማት፣ የሌማት ትሩፋት እና የኢንዱስትሪ መንደር ነው። የኢትዮጵያን ፀጋዎች አሳሳ ነው።
እሳቸው በውሏቸው ያሉንን ፀጋዎች መለየት ብቻ ሳይሆን ፀጋዎቹ ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዳይቀየሩ ያደረጉትን መሰረታዊ ችግሮች መለየት እና መፍትሄዎቻቸውን ማስቀመጥ ነው። በአይነ ህሊናቸው በጸጋዎች ውስጥ ሆኖ የተጎሳቆሉና የቆሸሹ መንደሮች፣ አካባቢዎች እና በዚህ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን በመመልከት የመውጫ መንገዱን በቁጭት ማለም ነው። ያለሙትን ወደ ተጨባጭ እቅድ ለውጠው በተግባር ወደ ውጤት መቀየር ነው።
በእሳቤያቸው እና በዕቅዱ ላይ በዙሪያቸው ያሉትን አመራሮች፣ የፓርቲውን አባላት፣ ቅን ዜጎችን በማስረዳትና በማስተባበር ወደ ተጨባጭ ተግባር ይቀይሩታል። ህዝቡንም ባለሃብቱንም በማቀናጀት ይበልጥ ውጤታማ ያደርጉታል።
በዚህም ማንም ሊክደው በማይችል መልኩ መንደሮች፣ አካባቢዎች፣ ከተሞች እየተቀየሩ ነው። ዜጎች ጥሪት እያፈሩ ነው። ኢኮኖሚው እያደገ ነው። ብቁ ተቋማት እየተገነቡ ነው። ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እመርታ እየታየ ነው። ኢትዮጵያም እያንሰራራች ነው፡፡ ሀቁ ይሄው ነው።
እኛ ኢትዮጵያውን ብቻ ሳንሆን የሌሎች ሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ቱሪስቶች እያደነቁት ነው፡፡ አንዳንዶቹም ልምድ ከኢትዮጵያ እያቀሰሙ ነው፡፡ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እየጎረፈ ነው፡፡ ይህ የውሎ ውጤት ነው፡፡ የስኬቱ ምንጭም በውሎው በተፈጠረው አውድ ላይ የተደረገ ቁርጠኛ ርብርብ ነው፡፡
ፈጣሪ የሰጠህን እውቀት፣ ክህሎት እና ፀጋ ለለውጥ፣ እድገትና ለብልጽግና መጠቀም በሚያስችል አውድ ላይ ውሎህን ከመሰረትክ በእርግጥም ስኬታማ ትሆናለህ፡፡ ውሎህን የሴራ ፖለቲካ፣ በአቋራጭ ወደ ስልጣን በመምጣት ግለሰባዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ ቆሞ ቀር የጽንፍና የጥላቻ አስተሳሳብ የተጠናወተው አውድ ውስጥ ካደረግከው አስተሳሰብህንና እይታህን የሚቀርጽህ፣ ማንነትህንም የሚበይነው እና ድርጊትህን የሚወስነው ይህ አውድ ነዉ፡፡
ይህ አውድ ባሪያው ያደርግሃል፡፡ “ማር ለአህያ አይጥማትም” እንደሚባለው ዓለምን ጉድ ያሰኘ ተዓምር ቢፈጠር አይጥምህም፡፡ እንደ ኮሶ ይመርሃል፡፡ያንገፈግፈሃል፡፡ ያንገሸግሽሃል። ከዚህ አውድ መላቀቅ የምትችለው ሩቅ አላሚ፣ ወገንህን ተመልካች፣ የአንድን አካባቢ ወይም ሀገር መሠረታዊ ችግሮች ሳይንሳዊና ጥባባዊ መርህና ህጎች በመከተል እና በብቃት በመለየት ተግባራዊ የመፍትሄ ሃሳብ ማፍለቅ ስትችል ነው፡፡
ጠብ መንጃ አንጋቾች፣ ቆሞ ቀር ፖለቲከኞች፣ ባንዳዎች እና አጫፋሪዎቻቸው ማድረግ ያልቻሉት ጉዳይ ይህን ነው፡፡ ምክንያቱም ውሎአቸውና እሱ የፈጠረው አውድ ይህን ማድረግ አይፈቅድላቸውም፡፡ ይህ እንዲነሳባቸው አይፈልጉም፡፡ ሰነፎችና ርዕይ አልባ ስለሆኑ፣ ሞክረውትም ስለማያውቁ ይኮሰኩሳቸዋል፡፡ ስለሆነም እንደ መፍትሔ የሚወስዱት የበጉን እረኛ ከበጎቹ ነጥሎ መምታት ነው፡፡ ከዚያም በጎቹን እንደፈለጉ ማድረግ ነው፡፡
ይህ የቅዠትና የምናብ መፍትሄም ከውሎአቸው የሚቀዳ ነው፡፡ ያልተረዱት ነገር እረኛው በጎቹን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ጠንቅቆ ማወቁን ነው፡፡ በጎቹም ቢሆኑ እረኛቸውን ላያስነኩ ምለው መገዘታቸውን ነው።
እነዚህ በውሎ አውዳቸው ምክንያት የቅዠት እስረኞች የሆኑ ባንዳዎች ይህ ምሳሌያዊ ንግግር እንኳ በእውናዊው ዓለም ስላሉ “በጎችና እረኛ” የተፃፈ ይመስላቸው ይሆናል። እናም ወዳጄ፣ ውሎህ እይታህን እንኳ ይወስነዋል፤ መፍትሔውም ውሎህን መምረጥ ወይም ማስተካከል ነው፡፡
አሁን አሁን ደግሞ “ከዐቢይ በኋላ” የሚባል ዲስኩርም እየሰማን ነው፡፡ ይሄም የውሎ ውጤት ነው፡፡ የበርካታ አስርት ዓመታት ቆሞ ቀር የፖለቲካ እሳቤ የወለደው የ“ሽግግር መንግስት መዝሙር” አውድ የፈጠረው ነው፡፡ አውዱ ውስጥ ያለው እሳቤ ቆሞ ቀር ግትር እሳቤ ነዋ!!
ወዳጄ ጭንቅ አይግባህ! ከዐቢይ በኋላማ ዐቢይ እራሱ ሀገሩን ለትውልድ ትውልዱን ለሀገር እያዘጋጀ ነው፡፡ ይህ እውነት መሆኑን እንዳትክድ ያለፉትን ሰባት ዓመታት እመርታዎች ተመልከት፤ ምን እንደተሰራ ቆጥሬ አልጨርስልህም።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የወያኔ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴን አጢነው ሰሞኑን አንድ ምጥን መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ “ያለፈውም ለማንም አልበጀ፣ አካባቢውንም ሀገርንም አልጠቀመም፤ትርፉ ኪሳራ ነበር፡፡ ወደ ግጭት ለመግባት የሚደረገው ሙከራ ሌላ ጉዳት ያመጣ ይሆናል እንጂ አይጠቅምም፡፡
ጥያቄያቹሁን በሰለጠነ አግባብና በህገ መንግስቱ መሠረት ጠይቁ፡፡ ተዉ የሚል መልዕክት፡፡” ይህን ተከትሎ በጠብ መንጃ አንጋቾች፣ ቆሞ ቀር ፖለቲከኞች፣ ባንዳዎች እና አጫፋሪዎቻቸው ሰፈርና መንደር ጩኸት በረከተ፡፡ ለምን? በዚያ መንደር ያለው አውድ ሰላም፣ ልማት፣ ብልጽግና፣ ከልመና መውጣት፣ ስንዴ፣ የሌማት ቱሩፋት…ወዘተ አጀንዳ አይደለማ!! በዚያ አውድ ትርፍ የሚገኘው ከግጭት ነው፡፡ ህግ እና ስርዓት ባለበት ወርቅ መዝረፍ አትችልማ!!
የማርሻሉ አውድ ደግሞ አስተማማኝ የመከላከል፣ ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር፣ የፌዴራል ስርዓቱ ጠባቂ እና የዜጎች ጥቅምና ደህንነት አስከባሪ ሰራዊት መገንባትን እንጂ መንደርተኝነትን የሚቀበል አይደለም፡፡
ይህ የውሎ ጉዳይ በማህበረሰቡ ውስጥም በተለያየ ሁኔታ ይገለፃል፤ ሰሞኑን የኪነጥበቡ ዓለም አንዱ አውድና መገለጫ በሆነው በሙዚቃ ኢንደስትሪው፣ ሙያተኞችን ነጥሎ የመምታት አባዜም የዚሁ የውሎ ጉዳይ ነው። ውሎህ አንተነትህን ይወስነዋል የሚባለው ለዚሁ ነው!!
ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025