ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስራ ዕድል ፈጠራ እና በገበያ ትስስር የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው የ2017 ዓ.ም የዕቅድ አፈፃፀምና የ2018 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሄዷል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ ፤ በ2017 በጀት ዓመት የስራ ዕድል ፈጠራ እቅድ ለመፈጸም በተቀናጀ መንገድ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በአገልግሎትና መሰል ዘርፎች በከተማና በገጠር የተሻለ የስራ ዕድል በመፍጠር የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ስራ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚልቁ ስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ከዕቅድ በላይ መፈጸም መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ በ55 ሺህ 510 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ወደ ስራ ለገቡ ወጣቶች ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ስልጠና መስጠቱንም አመልክተዋል።
የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከሌሎች አማራጮች ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማመቻቸት መቻሉን ጠቅሰው፤ የመስሪያና የመሸጫ ቦታም እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በሃገር ውስጥ እና በውጭ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን የገለፁት ደግሞ የቢሮው የዕቅድ ክትትል ባለሙያ አቶ ጌታቸው ጫኔ ናቸው።
የሃገር ውስጥ ገበያ ትስስሩም በቅዳሜና እሁድ ገበያ፣ ኤግዚብሽንና ባዛር በማዘጋጀት የተፈጠረ ሲሆን በቆዳና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ደግሞ የውጭ ገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልፀዋል።
በሃገር ውስጥ ከተፈጠረው የስራ ዕድል ባለፈም በውጭ ሃገር የስራ ስምሪት አስፈላጊውን የህይወት ክህሎት ስልጠና የወሰዱ ከ87 ሺህ በላይ ዜጎች በህጋዊ መንገድ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ የሁሉንም አካላት ትብብርና እገዛ የሚሻ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጠናከር እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በመድረኩ የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የ2017 ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 መሪ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025