አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ለውጥን ከአየር ንብረት ፖሊሲ እርምጃዎች ጋር በማጣጣም አይበገሬና ዘላቂ የምግብ ስርዓት ለመገንባት ትኩረት ማድረጓን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በአፍሪካ የምግብ ስርዓት ላይ ያተኮረ የአፍሪካ ሼፎች የውይይት መድረክ እና የፖሊሲ ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር አማካሪ ሃና አበበ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ስነ-ምህዳሮቿን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው።
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ጉዳት መከላከል የሚያስችላትን ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ በማውጣት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ፖሊሲዎቹና የህግ ማዕቀፎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች ሁሉን አቀፍ ምላሽ ለመስጠት መሰረት መጣላቸውን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓትን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ማጣጣም የሚያስችሉ የፖሊሲ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
ፖሊሲው የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርና ላይ ኢንቨስት ማድረግን፣ የተራቆቱ መሬቶችን ወደ ነበሩበት መመለስን፣ አነስተኛ አርሶ አደሮችን በተለይም ሴቶችንና ወጣቶችን ማብቃት ላይ እንደሚያተኩር አንስተዋል፡፡
በኢትየጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት በደን መልሶ ልማትና የተራቆቱ መሬቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የተሰራውን ውጤታማ ስራ ለአብነት ጠቅሰዋል።
"ኢስት አፍሪካን ሌጅስሌሽን አሴምብሊ" (EALA) የግብርና፣ የቱሪዝም የተፈጥሮ ሃብት ሊቀ-መንበር ፍራንሲሶ ዩዎማኩዜ በበኩላቸው፤ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ፖሊሲዎች ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ግብርና ይልቅ በሰፋፊ ግብርናዎች ላይ እንደሚያተኩሩ ተናግረዋል።
የሚታዩትን የፖሊሲ ክፍተቶች ለመሙላት አነስተኛ አርሶ አደሮችን የሚደግፉ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽና የአካባቢ የምግብ ሥርዓቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ ብዝሃ ህይወት መረብ ዳይሬክተር እና የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት የቦርድ አባል ፋሲል ገበየው(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ፍትሃዊና ዘላቂ የአፍሪካ የምግብ ስርዓት ለመፍጠር በትብብር መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ኢትየጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተለይ በአረንጎዴ ዐሻራ እየሰራች ያለው ስራ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡።
"ምግቤ አፍሪካዊ ነው'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባዔ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ፖሊሲ አውጪዎች ፣ የምግብ ባለሙያዎች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የልማት አጋር ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025