ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
በአፍሪካ መዲና የሚካሄደው ጉባኤ መወያያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በ2015ዓ.ም በጣልያን ሮም በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ አጀንዳዎች አፈጻጸም ይገኝበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሮሙ ጉባኤ ላይ ከተገኙ የሀገራት መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
በጉባኤው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና በስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማምጣት እየወሰደች ባለው የፖሊሲ እርምጃ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ ለስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎችን፣ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል ነበር።
አያይዘውም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በበጋ መስኖ በተለይም በበጋ ስንዴ ምርትና በሌማት ትሩፋት እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ለጉባኤው ማቅረባቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ ድል ፈጠራን ለማበረታታትም ሆነ በስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማድረግ አዲስና የተለየ የፋይናንስ ሞዴል ያስፈልጋል በማለት በአጽንኦት መናገራቸውም እንዲሁ።
በኒውዮርክ በተካሄደው የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የተቀመጡ ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግር አቅጣጫዎች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው ቢሆንም በፋይናንስ አቅርቦት፣ በዓለም አቀፍ ትብብር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም በትብብር በመስራት በኩል በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን ማንሳታቸው ይታወሳል።
በመሆኑም ሀገሮች በስርዓተ ምግብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በአነስተኛ እርሻ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ለዚህም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን እንዲያሳድጉና ለግብርና ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሰሩ መጠየቃቸውም ይታወቃል።
በሌላ በኩል የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ በሰበሰቡት ዓለም አቀፍ የልማትና የፍልሰት ኮንፍረንስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ ሀገራዊ ዕድገትን ማፋጠን የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋትና ድህነትን ለማቃለል፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰትን ለመቀነስ ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።
እንዲሁም የፍልሰት መነሻ ምክንያቶችን ለይቶ ለመቅረፍ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ አዳዲስ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋትና የክህሎት ግንባታን ማዕከል ያደረገ የስራ ስምሪት መተግበር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በጉባኤው የተገኙት የግብርና እና የፕላንና ልማት ሚኒስትሮች በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም፣ በተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮች ላይ የኢትዮጵያን የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት አቅርበው ነበር።
ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት በሚደረገው እንቅስቃሴ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጅ፣ በአመራር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ማላመድ ዙሪያ ያሉ የኢትዮጵያ ልምዶችም ቀርበዋል።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በጉባኤው ላይ የ160 ሀገራት ተወካዮች እንደሚገኙም ይጠበቃል።
የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ፣ የምግብ ስርዓት ሽግግር ሁለንተናዊነትና የተገቡ ቃሎችን ከመፈጸም አንጻር ያለውን የተጠያቂነት ስርዓት ማጠናከር ጉባኤው ትኩረት የሚያደርግባቸው ሀሳቦች ናቸው።
በሮም የተካሄደው የተመድ ስርዓተ ምግብ ጉባኤ ቃል የተገቡ ጉዳዮች አፈጻጸምም እንዲሁ ይገመገማል።
ኢትዮጵያም ከሮሙ ጉባኤ በኋላ አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግር ጉዞዋን የሚያጠናክሩ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ሁሉም ዜጋ ደህንነቱ የተረጋገጠና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የንጥረ ምግቦችን ብዝሃነት በሌማት ትሩፋት እውን ለማድረግ እየሰራች ነው።
የስርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታን ጨምሮ አካታችነትና ተደራሽነትን ዋና ማዕከላቸው ያደረጉ የአሰራር ማዕቀፎችም በመተግበር ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና በግብርናው ዘርፍ በተገበረቻቸው ሀገር በቀል ሪፎርሞች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የዘንድሮውን ጉባኤ እንድታስተናግድ አስችሏታል።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ለውጥ ውስጥ እየተወጣች ያለው የመሪነት ሚና በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት በስርዓተ ምግብ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መሆኗ ተመድ ዓለም አቀፉን ከፍተኛ ጉባኤ እንድታስተናግድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
በጉባኤው ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እያከናወነች ባለው ተግባር ዙሪያ ተሞክሮዋን ለዓለም ማህበረሰብ ታካፍላለች።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025