የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅምን በማጎልበት የግሉን ዘርፍ የኃይል ፍላጎትና አጠቃቀምን ማሳደግ ተችሏል-ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)

Jul 23, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅምን በማጎልበት የግሉን ዘርፍ የኃይል ፍላጎትና አጠቃቀም እንዲጨምር ማድረጉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የግሉን ዘርፍ ተዋናዮችን፣ፖሊሲ አውጪዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን በማሳተፍ በዘላቂ ልማት፣ በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊና በንግድ ዙሪያ የሚመክር የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ የግል ዘርፍ መድረክ ተካሂዷል፡፡


የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ለአካታች ፋይናንስና ልማት የብድር አገልግሎት ማመቻቸት፣የኢንቨስትመንት ከባቢ በኢትዮጵያ እና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የጀርባ አጥንት ነው፡፡

የሥራ ዕድል በመፍጠርና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂን የሚያንቀሳቅስ ሞተር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የኃይል ማመንጫዎች ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር በራሳቸው አቅም እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አስችሏል ብለዋል፡፡

ኃይል የማምረት አቅምን ከማጎልበትም ባለፈ የግሉ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና አጠቃቀም እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት 20 ሺህ 500 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት 17 ሺህ 500 ጊጋ ዋት ሰዓት እንደተሸጠ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በ2017 በጀት ዓመት 28 ሺህ 600 ጊጋ ዋት ሰዓት በማምረት 27 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት የሚደርስ ኃይል መሸጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

ይሄውም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ከማጎልበት ባለፈ የግሉን ዘርፍ የኃይል ፍላጎትና አጠቃቀም ማሳደጉ ማሳያ መሆኑን ተናገረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመሮችን በመስራት የኃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የነፍስ ወከፍ ፍጆታ በእጅጉ መጨመሩን ገልጸው፤ የግል ባለሃብቶች በታዳሽ ኃይል ልማት በመሰማራት ያለውን እምቅ አቅም ጥቅም ላይ እንዲያውሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት የባለሃብቱን ተሳትፎ ለማበረታታት ለሥራ ምቹ የሆኑ አሰራሮችና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማውጣት ትብብር እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.