ሮቤ ፤ሐምሌ 15/2017 (ኢዜአ)፡- በባሌ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የቦንድ ግዢ የንቅናቄ መርሃ ግብር እየተካሄደ መሆኑ ተገለፀ።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም የዞኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የቦንድ ግዢ የንቅናቄ መርሃ ግብሩ እየተካሄደ የሚገኘው ወደ ዞኑ የመጣውን የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ምክንያት በማድረግ መሆኑም ተጠቁሟል።
በባሌ ሮቤ ከተማ በተካሄደው የንቅናቄ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሐኪም አልይ የዞኑ ነዋሪዎች ባለፉት ዓመታት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥና የስጦታ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ለግድቡ ግንባታ ውጤታማነት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የቦንድ ግዢ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ አብዱልሐኪም እንዳሉት በየደረጃው የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የፀጥታ አካላት፣ ባለሃብቶችና መላው የዞኑ ነዋሪዎችን ለማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውንም ኃላፊው ገልፀዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የቦንድ ግዢ ከፈጸሙ ነዋሪዎች መካከል አቶ አደም ማህሙድ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለሶስተኛ ጊዜ የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የግድቡ ዋንጫ ወደ ዞኑ መምጣቱን ተከትሎ ለአራተኛ ጊዜ ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በቦንድ ግዢው የተሳተፉትና የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አባል የሆኑት ኮማንደር ሁሴን አብዲ በበኩላቸው የፖሊስ አባላት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በአገር ልማት ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የአሁኑን ጨምሮ በደመወዛቸው ለአራተኛ ጊዜ የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ተናግረው የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ወይዘሮ ከሪማ አህመድ በበኩላቸው የአንድነትና የጋራ አሻራ የሆነው የህዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ በግል ከመሳተፍ ባሻገር ሌሎችን በማስተባበር አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እንደሚጥሩም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የግድብ ግንባታው በመጠናቀቁ በመስከረም ወር 2018 ዓ/ም ሪባን ቆርጠን እናስመርቀዋለን ማለታቸው ይታወሳል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025