ነገሌ ቦረና፤ ሀምሌ 15/2017 (ኢዜአ )፡-በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ችግኝ በስፋት እየተተከለ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የቡናና ቅመማቅመም ልማት ባለሙያ አቶ ብርሀኑ ፈይሳ እንደገለጹት በዞኑ በተያዘው ክረምት ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የቡና ችግኝ ተከላ እየተከናወነ ይገኛል።
የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ እስካሁን ድረስ ከግብርና ምርምር ተቋማት የወጡ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ ዝርያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ እንዲሁም ድርቅና በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል አቅም ያለው ነው ብለዋል፡፡
የተሻሻሉ ችግኞች ከጅማ፣ ከይርጋለም እና ከአወዳይ ግብርና ምርምር ማእከላት የተለቀቁና ከተሻሻለ የአካባቢ ዘር የተገኘ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በአካባቢው እየለማ የሚገኘው ነባሩ የቡና ዝርያ በሄክታር ከ7 እስከ 9 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ሲሆን የተሻሻለው ዝርያ ከአንድ ሄክታር ከ10 እስከ 15 ኩንታል ምርት እንደሚገኝም በሰርቶ ማሳያ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ነባሩ የቡና ዝርያ ለመድረስ እስከ 7 ዓመታት የሚወስድበት ሲሆን የተሻሻለው የቡና ዝርያ ግን በአራት ዓመት ውስጥ ምርት መስጠት ይጀምራል ብለዋል።
የቡና ዝርያውም በግልና በመንግስት ችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጀ ሲሆን ችግኞቹንም ከዞኑ የአየር ጸባይ ጋር የማላመድ ስራ በጥንቃቄ መካሄዱንም አንስተዋል፡፡
በዘንድሮው የቡና ልማትና የችግኝ ተከላ ስራ ከ60 ሺህ የሚበልጡ የዞኑ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው በዞኑ 157 ቀበሌዎች የቡና ልማት እየተካሄደ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የዞኑን የቡና መሬት ሽፋን 177 ሺህ 280 ሄክታር ሲሆን በዘንድሮው የቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሽፋኑን የሚያሳድግ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዞኑ አዶላ ወረዳ የዶሌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመዳ ቡና፤ ከሌላ የግብርና ስራ ጎን ለጎን በቡና ልማት የ20 ዓመታት ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ተሻሽሎ የመጣው የቡና ችግኝ ዝርያ የምርት ጥራትና ብዛትን እንደሚያሳድግ ከልማት ጣቢያ ሰራተኛ ምክር ተቀብለው ዘንድሮ የተሻሻለ የቡና ችግኝ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እየተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚሁ ወረዳ የአንፈራራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደሰ ወኬ፤ በቡና ተክል ልማት የረጅም ዓመታት ልምድና ተሞክሮ እንዳላቸው ገልጸው የተሻሻለውን የቡና ችግኝ ዝርያ በመትከል እና ልማቱን በማስፋፋት ምርታቸውን የማሳደግ እቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025