የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል

Jul 22, 2025

IDOPRESS

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 14/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርታማነትን በማሳደግ የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

"የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ሃሳብ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በጋራ ያዘጋጁት አውደ ርዕይና ባዛር በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።


የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች አውደ ርዕዩንና ባዛሩን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ምርቶችን በማሳደግ ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።


አውደርዕዩ እና ባዛሩ መዘጋጀቱ ምርቶቹ የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ዕድል እንዲያገኙ ብሎም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የተለያዩ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማኑፋክቸርንግ፣ የቤትና የቢሮ መገልገያ እና ሌሎች ምርቶችም በስፋት መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

"ምርት ማምረት ብቻ ሳይሆን በገበያ ላይ ተፈላጊነት ያላቸው መሆን አለበት" ያሉት ሃላፊዋ ምርቶችን በአይነት፣ በጥራትና በመጠን አሳድጎ ለገበያ በማቅረብ የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በባዛሩ ቡና፣ ማሾ እና ሰሊጥን ጨምሮ ከሰባት በላይ የወጪ ምርቶች መቅረባቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ሰናይት ፣ ላኪዎች ይህን ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።


የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ በበኩላቸው ምክር ቤቱ በክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

አውደርዕዩና ባዘሩ የገበያ ትስስርን ከመፍጠር ባለፈ ጅምላ ነጋዴዎች ወደ ወጪ እና ገቢ ምርቶች ንግድ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ዕድል ይፈጥራል።

በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነው የአርባ ምንጭ አዞ ራንች የአዞ ቆዳ እና ሥጋ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ምርት አቅራቢና የራንቹ የዱር ህይወት አያያዝ ባለሙያ ወይዘሮ ነፃነት ግርማ ናቸው።


ዝግጅቱ ለራንቹ የገበያ ትስስር የሚፈጥር ብሎም ሸማቹ ማህበረሰብ ምርቶችን በአንድ ማዕከል እንደያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ቤሬ ሐር ምርቶች ማህበር ማርኬቲንግ ባለሙያ ወይዘሪት ክብረወሰን በላይነህ ማህበሩ በእጅ ጥበብ የተሠሩ የሐር ምርት አልባሳትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል ብላለች።


አውደ ርዕዩ ለማህበሩ ተጨማሪ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሳ ዜጎች የሀገራቸውን ምርት በመጠቀም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁማለች።

ክልል አቀፍ አውደር ርዕዩና ባዛሩ ከዛሬ ጀምሮ ለ15 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ150 በላይ ነጋዴዎችም ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.