የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በኦሮሚያ ክልል በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት እና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል

Jul 21, 2025

IDOPRESS

አዳማ ፤ሀምሌ 12/2017(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት እና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

እየተካሄደ በሚገኘው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸሙን ያቀረቡት የክልሉ ፕሬዚዳንት በክልሉ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት እና በፕሮጀክቶች አፈጻጻም ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።


በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለይ ለውጪ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ለሚያመርቱ ኢንቨስትመንቶች በተሰጠው ትኩረት ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ተኪ ምርቶችን ከማምረት አንጻርም አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው በበጀት አመቱ ከ20 ሺህ በላይ ኢንቨስትመንቶችን መቀበል ተችሏል ብለዋል።

ከነዚህ መካከል 12 ሺህ የሚሆኑ ኢንቨስትመንቶች 341 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ እና ለበርካታ የክልሉ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በስፋት ወደ ስራ ከገቡ አንቨሰትመንቶች መካከል አርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራት ድርሻም ትልቅ እንደነበረ ነው የገለጹት።

ከስራ እድል ፈጠራ አንጻርም በበጀት ዓመቱ ለ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ በዚህም የክልሉ ወጣቶች በኢኮኖሚው ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መቻሉን ተናግረዋል።

ከተሞችን የመሸጫ ብቻ ሳይሆን የማምረቻ ማእከል ከማድረግ አንጻርም የወተት ላሞች፣ የዶሮ፣ የአሳማ እንዲሁም የአሳ እርባታ ክላስተሮች ወደ ስራ ገብተዋል።

ከተሞችን ለኑሮ ምቹ እና ሳቢ ለማድረግ በተከናወነ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ መቀየር የተቻለ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታቸው ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ200 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ ገቢውም የተሰበሰበው ከመደበኛ ገቢ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ እና ከልዩ ልዩ የገቢ አርእስቶች መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ስራዎች፣ ሀገ ወጥ ንግድን ከመከላከልና መቆጣጠር እና ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከልም አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ በሙስናና ብልሹ አሰራር የተመዘበረውን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰው በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ የአገልግሎት አሰጣጥና ግዥን ለማዘመን የዲጂታላይዜሽን አሰራርን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መሰራቱንም አስታውቀዋል።

የተመዘበረ ንብረትና በሙስናና ሌብነት የተተገኘ ሀብት ከማስመለስ ረገድ 106 የመኖሪያ ቤቶች፣ 92 የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ሶስት ህንፃዎችና 33 ተሽከርካሪዎች መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ካሬሜትር ቦታ የከተማ መሬት እንዲሁም 376 ሄክታር የገጠር መሬት ወደ መንግሥት የመሬት ካዝና እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

የጨፌው አባላትም የክልሉ መንግስት በበዙ ዘርፎች አበረታች ስራዎች ማከናወኑን አንስተው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል።

በተለይ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የበለጠ ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ ችግር በመቀረፉ መንግስትን አመስግነው የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ አሁንም መንግስት የህግ ማስከበር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.