የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የንግዱ ማህበረሰብ የዘርፉን ሥራ በፍትሃዊነት በማሳለጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን እንሰራለን - እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

Jul 21, 2025

IDOPRESS

ሆስዕና ፤ ሐምሌ 11/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የንግዱ ማህበረሰብ የዘርፉን ሥራ በፍትሃዊነት በማሳለጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የ2017 ማጠቃለያ ጉባኤና የንግድ ሳምንት ባዛር በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል ፡፡


በዚህ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የሸማቹን ፍላጎትና የአምራቹን አቅርቦት በማጣጣም የንግዱን ሥርዓት ፍትሐዊና የተሳለጠ ለማድረግ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን ፣ ገበያን ለማረጋጋት እና እጥረትን ለማስቀረት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ፡፡

የንግዱን ማህበረሰብ ችግር ለይቶ ለመፍታትና ተወዳዳሪ እንዲሆን እንሰራለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የንግዱ ማህበረሰብም ህብረት በመፍጠር ለትላልቅ ሥራዎች ልምድ ማዳበር እንዳለባቸውን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው፤ የንግድ ሥርዓቱን ሕጋዊና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ የቁጥጥር ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።


በዚህም ባለፈው የበጀት ዓመት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አመልክተው፤ ‎ለአብነት በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘ ከ300 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና ህግን የተላለፉ ማደያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

‎አምራችና ሸማችን በማቀራረብ ገበያን በማረጋጋትና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትን በመዘርጋትም እንዲሁ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ‎በተለይ በከተሞች የሰንበት ገበያዎችን ቁጥራቸውን በማሳደግ አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ እንዲገናኙ ማድረግ እንደተቻለ አብራርተዋል ።

ከባዛሩ ተሳታፊዎች መካከል ከሀላባ ዞን አቶቴ ኡሎ ወረዳ የመጡት አቶ አብደላ ሀሰን፤ በተሰማሩበት የንብ ማነብ ሥራ የሚያገኙትን የማር ምርት በራሳቸው ሱቅና ባዛሮች ላይ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው፤ በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ከተጀመረ በኋላ ሥራቸውን በስፋትና በዘመናዊ መንገድ መከወን እንደቻሉ ተናግረዋል።


‎ዘንድሮ ብቻ ሰብስበው ባቀረቡት የማር ምርት 950 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውንም አውስተዋል።

‎በጉራጌ ዞን አድማስ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ግብይት ክፍል አስተባባሪ ወይዘሮ ዐባይነሽ ኪሮስ ፤ ዩኒየኑ ከአባላት ግብዐት በመሰብሰብ የተጣራ የኑግ ዘይት እያመረተ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ ጠቁመው፤ የአካባቢውን ገበያ በማረጋጋትም አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


በመርሀ ግብሩ ላይ የተቋማት አመራሮችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የተሳተፉ ሲሆን፤ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሴክተሩ አደረጃጀቶች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.