የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ የታክስ ማጭበርበርን በማስቀረት የገቢ አማራጮችን የሚያሰፋ ነው

Jul 18, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፦የተሻሻለው የገቢግብር አዋጅ የታክስ ማጭበርበርን በማስቀረት የገቢ አማራጮችን እንደሚያሰፋ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን አፅድቋል።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ የማሻሻያ አዋጁ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል።


የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በዚሁ ጊዜ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የገቢ ግብር አዋጅ ዲጂታል ኢኮኖሚውን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በአዋጁ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ከዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

የታክስ መሰረትን በማስፋት የመንግስትን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማሳደግ የታቀደው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

እንደ ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገለጻ የማሻሻያ አዋጁ የታክስ ማጭበርበርን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

ይሁንና እውነተኛ ኪሳራ የገጠማቸው ግብር ከፋዮች ጉዳያቸው በአግባቡ ተፈትሾ መፍትሄ የሚያገኙበት አሰራርም መዘርጋቱን ነው የገለጹት።

የምክር ቤቱ አባላት የማሻሻያ አዋጁ አገሪቷ መሰብሰብ ያለባትን ገቢ አሟጣ መጠቀም እንደሚያስችል ተናግረው፤ በሌላ በኩል የአዋጁ ማሻሻያ በአጭር ጊዜ መከናወኑ ተገቢ ነው ወይ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።


የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ የማሻሻያ አዋጁ ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀ ጥናት እንደተደረገበትና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

ተለዋዋጭ የሆነውን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የገቢ ግብር እንደ ሀገር ለታቀደው የኢኮኖሚ እድገት እውን መሆኑ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ አዋጁን ማሻሻል ተገቢና አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በተለይም የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከልና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የአዋጁ መሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

የማሻሻያ አዋጁ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

መንግስት የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋዮችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንና ከገቢ ግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚፈጥር ጫና አለመኖሩንም አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጁን በአምስት ተቃውሞ፣ በ12 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በተያያዘም ምቹ የስታርታፕ ምህዳርን በመገንባት ውጤታማና ስኬታማ በማድረግ በዚህም ኢንዱስትሪዎችንና ኩባንያዎችን በማፍራት ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።


ስታርታፕ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና ያለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.