የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት የተያዘው ውጥን አፈጻጸም...

Jul 18, 2025

IDOPRESS

አስራ ሰባቱ የዘላቂ ልማት ግቦች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ማጽደቃቸው ይታወቃል።

ከእነዚህ የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል በግብ ሁለት ላይ የሰፈረው እ.አ.አ በ2030 ረሃብን ማጥፋት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማሻሻል እና ዘላቂ ግብርናን ማረጋገጥ ይገኝበታል።

ግቡ ሁሉም ዜጎች በተለይም በተጋላጭ ሁኔታዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተመጣጠነና በቂ ምግብ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

ምግብ ለሁሉም የሚለው ውጥንም ከዘላቂ ልማት ግቦች ረሃብን የማጥፋት እቅድ የሚቀዳ ነው።

በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ሴቶችና ህጻናት ልዩ ትኩረት እንደሚያሻቸው ተቀምጧል።


ሁሉንም አይነት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን መግታት፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ምርትና ገቢ ማሳደግ እንዲሁም ዘላቂ የምግብ ስርዓትን መገንባት በግቦቹ ስር የተቀመጡ እቅዶች ናቸው።

ዘላቂ የምግብ ስርዓትን የሚያስቀጥሉ አሰራሮችን መከትልና ለከባቢ አየር ተስማሚ የሆኑ የግብርና ስራዎችን ማበረታታት እንደሚገባም ተቀምጧል።

የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ፈተናዎችን የሚቋቋሙ ዘላቂ የግብርና አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባም በምክረ ሀሳብ ደረጃ ተጠቁሟል።

የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት የኢንቨስትመንት መጠንን ማሳደግ፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያላቸውን የንግድ አሰራሮች መቀየርና አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የመሬት፣ ቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲሁም ለገበያ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።

የዘላቂ ልማት ግቦች ግብ ሁለት ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት የዓለምን የምግብ ስርዓት በመሰረታዊነት መቀየር እንደሚገባ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርቶችና ገለልተኛ ጥናቶች ረሃብን ለማጥፋት እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ቀላል ሊባሉ የማይችሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ያመለክታሉ።

ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ በታዩ መሻሻሎች በተለይም ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ህጻናት ላይ ያለውን መቀጨጭ እና መቀንጨር አበረታች ሊባል በሚችል መልኩ መቀነስ ተችሏል።


የምግብ ስርዓቶች አይበገሬ ቁመና እንዲኖራቸው በተከናወኑ ስራዎች በስርዓተ ምግብ ሽግግር ላይ መጠነኛ ለውጦች መታየታቸው ተመላክቷል።

የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ድህነት ቅነሳ ላይ ከአህጉር አህጉር ቢለያይም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውም እንዲሁ።

ይሁንና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እጥረት(ምግብ ማጣት እና ከልክ በላይ መወፈር)፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የረሃብ ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣት፣ የምርታማነት መቀነስ፣ የስራ እድል አለመኖር፣ ለጤና የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ አለማግኘትና የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ግቡ እንዳይሳካ ፈተና ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ረሃብን የማጥፋት የዘላቂ ልማት ግቦች የትግበራ ማጠናቀቂያ ጊዜ አምስት ዓመታት ቀርተውታል።

ዓለምን እየገጠሟት ያሉ ተደራራቢ ችግሮች ግቡን ለማሳካት ከፍተኛ ጋሬጣ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

የምግብ ስርዓቶችን ዘላቂና አይበገሬ ማድረግ፣ የፋይናንስ አቅርቦት መጨመር እንዲሁም አማራጮችን ማስፋት፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ የምግብ አምራቾችና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በፋይናንስ፣ በአቅም ግንባታ መደገፍ፣ የማህበራዊ ዋስትና ስርዓት አድማስን ማስፋት እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማሳደግ ግቡን ለማሳካት በአፋጣኝ መከወን ያለባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ሰላምን ማረጋገጥና ግጭቶችን ከምንጫቸው ማድረቅ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ትብብር በማጠናከር ተጠያቂነትን ማስፋት እንደሚገባም ምክረ ሀሳባቸውን ይለግሳሉ።

ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017ዓም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከዓለም ረሃብን የማጥፋት ውጥን ለማሳካት ያሉ እድሎች፣ ፈተናዎች እና ቀጣይ የተግባር ምላሾች ላይ ይመክራል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.