ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤው የሚዘጋጀው በኢትዮጵያ እና በጣልያን መንግስታት የጋራ ትብብር ነው።
የስርዓተ ምግብ አካታችነት፣ የጋራ ተጠያቂነትና ኢንቨስትመንት የጉባኤው የትኩረት ማዕከሎች ናቸው።
ከዋናው ጉባኤ በተጓዳኝ 31 የጎንዮሽ ሁነቶች ይካሄዳሉ።
የጎንዮሽ ሁነቶቹ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ስኬቶች፣ ፈተናዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ ይደረግባቸዋል።
የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን እሳቤን የማጉላትና የባለድርሻ አካላትን አጋርነት የማጠናከር ግብ አላቸው።
ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከሚከናወኑት 31 የጎንዮሽ መድረኮች መካከል ሁለቱ በኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪነት የሚካሄዱ ናቸው።
የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) ጋር በመተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እና ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ የምግብ ስርዓት ግንባታ የሚያስፈልግ ኢንቨስትመንትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት አዘጋጅተዋል።
ሁነቱ ኢትዮጵያ የግብርና ምርትን ከኢንዱስትሪ ሂደት ጋር በማስተሳሰር የግብርና ጥሬ ግብዓቶችን ወደ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች በመቀየር የምግብ ስርዓቱን ለመለወጥ የያዘችውን ግብ፣ ለውጥ እና አቅም የሚያሳይ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት መረጃ ያመለክታል።
መንግስት ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች(አግሮ ኢንዱስትሪ) ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች እንደሚቀርቡም ተመድ አስታውቋል።
ዲጂታላይዜሽንና ግብርናው የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የግብርና ምርቶችን እሴት ከማሻሻል፣ ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ እና የገበያ ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ ያላቸው ሚናም ይዳሰሳል።
በውይይቱ ፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ የመንግስት አካላት፣ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት፣ የተመድ ኤጀንሲዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ይሳተፋሉ።
ሁለተኛው ሁነት የእንስሳት ጤና ኢኒስቲትዩት ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ(አይኤኢኤ) እና የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) በጋራ ያዘጋጁት ነው።
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ(አይኤኢኤ) የብሔራዊ እንስሳት ጤና ምርመራ ቤተ ሙከራዎች ኔትወርክ(ቬትላብ ኔትወርክ) የእንስሳት እና የጀርባ አጥንት ካላቸው እንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች በመለየት እና በመከላከል እንዲሁም የምግብ ደህንነትን ለማሻሻል ያላቸው ሚና ውይይት እንደሚደረግበት ከኢኒስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ፣ ቦትስዋና፣ ቱኒዚያ እና ኮትዲቭዋር የስኬት ተሞክሯቸውን ያቀርባሉ።
ሁነቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂዎችና ቀጣናዊ ትብብር የምርመራ አቅምን፣ የበሽታ ቅኝት እና የክትባት ጥራትን በማሻሻል ረገድ ያላቸው ሚና ይዳስሳል።
የሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎን ከግምት ያስገባ ምክክር እንደሆነም ተገልጿል።
ሳይንስን መሰረት ያደረጉ የቁም እንስሳት ጤና ስርዓቶች ያላቸው የጤና እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታዎች እንዲሁም በአፍሪካና እስያ የማይበገር ስርዓተ ምግብ መገንባት የሚያስችሉ ዘላቂ የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚቀርቡም ተመድ አስታውቋል።
የስርዓት ምግብ ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን፣ የስርዓተ ምግብ ኢንቨስትመንት፣ የመንግስት እና የግል አጋርነት፣ የመሬት ጤና ጥበቃ፣ እርሻን ማዘመን፣ የሀገራት የስርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ መቀንጨርን መከላከል፣ ሀገር በቀል የምግብ እሴት ሰንሰለት፣ የዘር ዝግጅት እና ስርዓት፣ የቤተሰብ ግብርና እና አርሶ አደሮች በስርዓተ ምግብ ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ቀሪዎቹ 29 ሁነቶች የሚያተኩሩባቸው አበይት ሁነቶች ናቸው።
በተጨማሪም የጉባኤው ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ሽግግር ያከናወነቻቸውን ውጤታማ ተግባራትን እንደሚጎበኙም ተመላክቷል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025